7ኛው የደቡብ ጎንደር ዘመናዊ ስፖርት ሻምፕዮና በወረታ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

0
307

ሰባተኛው የመላው ደቡብ ጎንደር ዘመናዊ ስፖርት ሻምፒዮና ከጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በወረታ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በውድድሩም ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የውድድሩ ዓላማ ለመላው የአማራ ክልል ዘመናዊ ስፖርት ሻምፕዮና ዞኑን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለመመልመል ያለመ ነው፡፡

ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ለመላው አማራ ስፖርት ሻምፕዮና ዞኑን የሚወክሉ ብቁ ስፖርተኞችን እየመለመሉ መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ስፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሥጋናው አግማሴ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

አራተኛ ቀኑን የያዘው የመላው ደቡብ ጎንደር ዘመናዊ ስፖርት ሻምፕዮና እስካሁን የተካሄዱ ውድድሮች ስፖርታዊ ጨዋነትን የተላበሱ መሆናቸውን አቶ አግማሴ ተናግረዋል፤ ለዚህም የወረታ ከተማ በጎ አድራጊ ወጣቶችን አመሥግነዋል፡፡ የዞኑ ስፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትም ለስፖርታዊ ጨዋነት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ተገልጧል፡፡

በውድድሩ ከ15 የገጠር ወረዳዎች እና አምስት የከተማ አስተዳደሮች ከ1 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በ15 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች እየተካሄዱ ነው፡፡

ሰባተኛው የመላው አማራ ዘመናዊ ስፖርት ሻምፕዮና ከየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በወልድያ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here