ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ ከ5 ሚሊዮን 218 ሺህ በላይ ወጣቶችን በ13 የሥራ መስኮች ለማሰማራት ማቀዱን የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
መነሻው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የክረምት ወራት የረፍት ጊዜያት ጋር ተያይዞ ይነሳል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡ ተማሪዎቹ በየአካባቢያቸው በክረምት ወራት የሚያሳልፉትን የረፍት ጊዜ ለተከታዮቻቸው የማጠናከሪያ ትምህርት ለተማሪዎች ይሰጡ ነበር፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአይነቱ እና በተደራሽነቱ እየሰፋ የመጣው የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ ተዘጋጅቶለት እና ባለቤት ተሰጥቶት በመንግሥት መሸፈን ያልተቻሉ የዜጎችን ማኀበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ክፍተቶች የሚሞላ በጎ ተግባር ኾኗል፡፡ ከዚያ ባሻገርም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ዓመቱን በሙሉ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ታስቦ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲጠናቀቅ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየቀጠለ መሠረታዊ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ የአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ጥገና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሸፈኑ ተግባራት ኾነዋል፡፡ በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 62 በመቶ የክልሉ ወጣቶች ተሳታፊ ይኾናሉ ያሉን የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ ተሾመ ፈንታው ናቸው፡፡
5 ሚሊዮን 218 ሺህ 244 ገደማ ወጣቶችን ያሳትፋል የተባለለት የዘንድሮው የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 13 ዋና ዋና ተግባራትን ያቀፈ እንደኾነ ምክትል ቢሮ ኅላፊው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡ አረንጓዴ አሻራ፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋዊያን መኖሪያ ቤት ጥገና እና መሰል የተለመዱ ተግባራት ይከናወናሉ ያሉት አቶ ተሾመ 13ኛው ተግባር ግን በአዲስ የመጣ ሙያዊ አገልግሎት ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች ብቻ ሳይኾኑ የተለየ ሙያ እና ክህሎት ያላቸው ዜጎች ሙያቸውን መሠረት አድርገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ የመጣ ተግባር ቢኾንም ውስንነቶች ይስተዋላሉ ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው ተግባሩን የአንድ ተቋም ኅላፊነት አድርጎ ማየት፣ የግብዓት አቅርቦት ውስንነት እና ወጣቶችን በአግባቡ ተቀብሎ አለማስተናገድ ያጋጠሙ ፈተናዎች ነበሩ ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ሀገር 20 ሚሊዮን ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 51 ሚሊዮን ዜጎች ማኀበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚገኘው ማኀበረሰባዊ ትሩፋት ባሻገር ወጣቶች ሀገራቸውን በአግባቡ እንዲረዱ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!