ባሕርዳር: መጋቢት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 55ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ ፣የኢኮኖሚ ልማት እና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ስብሰባው “የአፍሪካ መልሶ ማገገም እና ለውጥን በማፋጠን ኢ-ፍትሐዊነትና ተጋላጭነትን መቀነስ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።
በስብሰባው መክፈቻ ላይ የኮሚሽኑ አባል ሀገራት የፋይናንስ፣ እቅድ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች እና ተወካዮች፣የተመድ ተቋማት ኃላፊዎች፣የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መደበኛ ስብሰባው ለሶስት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
ባለሙያዎቹ በአፍሪካ ያለውን ድህነት እና ኢ-ፍትሐዊነት እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ቀጣናዊ ትስስር ላይ ያሉ ለውጦች ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ተወያይተው ባቀረቧቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሚኒስትሮች ስብሰባው ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!