500 ሽህ ብር ጉቦ በመቀበልና የተለያዩ ሐሰተኛ ስሞችንና ሰነዶችን በመጠቀም ሲያጭበረብር የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

0
238

500 ሽህ ብር ጉቦ በመቀበልና የተለያዩ ሐሰተኛ ስሞችንና ሰነዶችን በመጠቀም ሲያጭበረብር የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር
መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተለያዩ የሥራ ድርሻ፣ አድራሻ፣ ስምና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀምና
በማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪው ስንታየሁ ቢርጉ ካየና፣ ስንታየሁ ተመስገን አበራ እና ስንታየሁ ደምሴ የተባሉ ስሞችን በመጠቀም የማጭበርበር
ተግባር ሲፈፅም መቆየቱን በፋይናንስና ንግድ ነክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ምርመራ
ኀላፊ አቶ ሽመልስ ጥበቡ ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ የካ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በፈጸማቸው ሕገወጥ ተግባራት የተለያዩ የክስ
መዝገቦች ተከፍቶበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት፣ ማታለልና በባለስልጣን ስም መነገድ ግለሰቡ ከተጠረጠረባቸው ወንጀሎች መካከል
እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡
ግለሰቡ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ እንደሌለው የሚናገርና የመኖሪያ አድራሻውን በመቀያየር የማጭበርበር ተግባር ላይ መሰማራቱን
ነው የገለጹት።
በሐሰተኛ መታወቂያው ላይ የፕሮቪዥን ኀላፊ እንደሆነ የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ሲገለገልበት መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሥራ ድርሻው መርማሪ መሆኑን የሚገልጽ ሐሰተኛ መታወቂያ አስወጥቶ ሲገለገል መቆየቱን ፖሊስ
ባደረገው ምርመራ እንደደረሰበት ተገልጿል፡፡
በወንጀል ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ብርበራ ሲደረግ እንደ ጠቋሚና ተባባሪ ሆኖ በመቅረብ የከፍተኛ መንግሥት ባለስልጣናትን
ስም እየጠራ ጉቦ እንደሚጠይቅ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አመላክቷል፡፡
ተክለብርሐን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሊዘጋ ነው ወይም ሊታገድ ነው ብሎ በማስፈራራት 500 ሺህ ብር ጉቦ መቀበሉንና
በሕገወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብም ለማሸሽ ሲል ወደ ባለቤቱ የሂሳብ ደብተር ሲያስተላልፍ እንደነበር ፖሊስ በማስረጃ
ማረጋገጥ መቻሉን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
ከቴሌ ኮምዩኒኬሽን የራሱ ባልሆነና ስንታየሁ ደምሴ በሚል ስም የሐሰተኛ መታወቂያ ሲም ካርድ በማውጣት ሲጠቀም መቆየቱን
ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰቡ ሲጠቀምባቸው የነበረው መታወቂያዎች ሁሉ ሐሰተኛ መሆናቸውን ፖሊስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር
በመሆን ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡም ኀላፊው አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ በግለሰቡ ላይ ባደረገው ክትትል ግለሰቡን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር
ስር አውሎታል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮም የክስ መዝገቡን ለሚመለከተው ዐቃቤ ሕግ እንደላከ
አስታውቋል፡፡
ግለሰቦች የሕግ አስከባሪ አካል ነኝ በማለት ወደ ሰዎች መኖሪያ ቤት ሲሄዱም ይሁን ምርመራ ሲያከናውኑ ኅብረተሰቡ
ማንነታቸውን የማጣራት ልምድና ባህል ሊኖረው እንደሚገባ አቶ ሽመልስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m