ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ንጋት ኮርፖሬት በ2022 የላቀ አፈፃፀም ላላቸው ኩባንያዎቹ እውቅና እየሠጠ ነው። በእውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ የንጋት ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መኮንን፣ የንጋት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምላኩ አሥረስ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የንጋት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምላኩ አሥረስ (ዶ.ር) ንጋት ኮርፖሬት የአማራ ሕዝብ ሀብት ነው ብለዋል። ንጋት ኮርፖሬት የአማራ ክልል የልማት አቅም ኾኖ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። ንጋት በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው 15 ኩባንያዎች በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር አልሚ ባለሀብቶች በሽርክና የተመሠረቱ 4 ኩባንያዎች፣ 4 ባንኮች፣ 2 ኢንሹራንስ፣ 3 በሚዲያ ዘርፍ ድርሻ አለው ነው ያሉት። በግንባታና በተለያየ የፕሮጄክት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሥድስት ፕሮጄክቶችን እንደሚያስተዳድርም ተናግረዋል።
ንጋት የክልሉን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ የትርፋማነት መጠኑን በመጨመር አዎንታዊ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ በንጋት ኮርፖሬት ታሪክ ትልቁ እና የመጀመሪያው ትርፍ የተመዘገበበት ነውም ብለዋል። ፈተናዎችን በማለፍ በፅናት በመቆም ውጤታማ ሥራ መሥራቱንም ተናግረዋል።

ንጋት ኮርፖሬት በ2014/ 2015 በጀት ዓመት 36 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለማኅበራዊ ሥራ ማዋሉንም ገልጸዋል።
የንጋት ተቋማዊ ፍልስፍናዎች ልማት የአማራ ክልል ሕዝብ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የተገነዘበ ነውም ብለዋል። ንጋት ኮርፖሬት በ2050 በአፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሽግግር የሚያመጣ የዘላቂ በጎ አድራጎት ተቋም የመሆን ራዕይ እንዳለውም አብራርተዋል።
የአማራ ክልልን የእርሻ ልማት ሥራ ለማዘመን 14 ሺህ የመስኖ ፓምፖች፣ 117 ትራክተሮች፣ ከ200 በላይ የመውቂያና የማለስለሻ መሳሪያዎችን አቅርቧል ነው ያሉት። በሠራው ሥራ በግብርናው ዘርፍ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት።
ንጋት ኮርፖሬት በትራንስፖርት ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም ገንብቷልም ብለዋል። ዓላማው የአማራን ሕዝብ በልማት ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል። የንጋት ኮርፖሬት ሀብት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ተናግረዋል። ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በታማኝ ግብር ከፋዮች ከተሸለሙ 11 ኩባንያዎች መካከል ሥድስቱ የንጋት ኮርፖሬት መሆናቸውንም አንስተዋል።
የልማት አውታርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ንጋት ኮርፖሬት ከተወሳሰቡ ችግሮች እየወጣ ትርፋማ እየሆነ ያለ ኩባንያ ነውም ብለዋል። የአማራ ክልልን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ አልሞ እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!