300 በላይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በቅጣት ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉን የፌደራል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

0
64
300 በላይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በቅጣት ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉን የፌደራል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ባሕር ዳር: የካቲት12/2013 ዓ.ም (አብመድ) የተቋማት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
በፌደራል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አክሊሉ ሙሉጌታ እንዳሉት የፌደራል ተቋማት፣ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በበጀት ዓመቱ እንዲሰሯቸው ከተቀመጡ 9 ነጥቦች ውስጥ የሀብት ምዝገባ በዋናነት ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ ነበር። በዚህም ከ537 ተቋማት 354ቱ ሙሉ በሙሉ የሃብት ምዝገባ ሥራ ማከናወናቸውን ነግረውናል። የተወሰኑ ተቋማት እስከ 99 በመቶ የሃብት ምዝገባ ሥራ አከናውነዋል ብለዋል።
በፌደራል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ተቋማት ደግሞ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ከሃብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን አቶ አክሊሉ አንስተዋል።
የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ ባለፈው ወር መጨረሻ መጠናቀቁን የገለጹት ዳይሬክተሩ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ተቋማት ውጭ ያሉ ተቋማት በአስገዳጅነት በቅጣት እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በፌደራል ደረጃ ሃብት ያላስመዘገቡ ከ300 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በቅጣት እንዲያስመዘግቡ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በተቀመጠው የቅጣት ጊዜ ሃብታቸውን ያላስመዘገቡትን ደግሞ ለፖሊስ እና ለጠቅላይ አቃቢ ሕግ ሪፖርት በማድረግ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ፤ ያላስመዘገቡበት ምክንያትም ለምርመራ ሥራ ይውላል ነው ያሉት፡፡
ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ተሿሚ እና የመንግሥት ሠራተኛ ሃብት የማወቅ መብት እንዳለው ነግረውናል፡፡ ስለ ግለሰቡ የሚያውቀውን መረጃ ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ግለሰቡ ያጋለጠው መረጃ ትክክል ከሆነ ደግሞ ከተገኘው ሃብት ላይ 25 በመቶ ለጥቆማ አቅራቢው ግለሰብ እንደሚሰጥና የሕግ ከለላ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በ6 ወሩ ለሃብት ምዝገባ የተሰጠው ትኩረት ለሌሎች ተግባራት አለመሠጠቱ እንደ ድክመት ተነስቷል።
የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅም አንዱ የውይይት ነጥብ ሆኖ ቀርቧል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት በሙስና ላይ ከነበረው የሕግ ማስፈጸም ሥራ ወጥቶ መከላከል ላይ በማተኮሩ ሕጉን ማሻሻል አስፈልጓል።
በተሻሻለው አዋጅም ከዚህ በፊት ተጠሪነታቸው ለተቋማት ኀላፊዎች የነበሩ የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ለሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሆን ተደርጓል።
በተሻሻለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ መመሪያ፣ በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ በአሠራር ስርዓት ጥናት አተገባበር እና በአስቸኳይ የሙስና መከላከልና አተገባበር ላይ ገለጻ ተደርጓል።
ኮሚሽኑ ለፌዴራል እና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተቋማት ግምገማዊ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here