29 ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

0
141

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በ2012 ዓ.ም 44 ሚሊዮን 195 ሺህ 685 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ደግሞ 29 ሚሊዮን 71 ሺህ 208 ሜትር ኪዮብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አለባቸው አሊጋዝ እንደነገሩን ከተዘጋጀው ውስጥ 9 ሚሊዮን 967 ሺህ 826 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በ212 ሺህ 490 ሄክታር ማሳ ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ 588 ሺህ 394 አርሶ አደሮች መሣተፋቸውንም አቶ አለባቸው አንስተዋል፡፡ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያው ሲዘጋጅ ሰፊ አረንጓዴ ዕፅዋት እና የእንስሳት ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የአርሶ አደሩ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን አስገንዝበዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም 40 ሚሊዮን ኪዩብ ሜትር የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ አቶ አለባቸው ከጥራት አንፃር በዚህ በጀት ዓመት የተዘጋጀው ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ጥሩ የሚባል የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ እንዳዘጋጁ ማረጋገጣቸውንም አቶ አለባቸው ተናግረዋል፡፡

ጥራት ያለው የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ እንዲዘጋጅ የግንዛቤ ፈጠራ፣ ድጋፍና የልምድ ልውውጥ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here