አቢዮተኛው የብርዕር ሰው ሲታወስ!

0
291
አቢዮተኛው የብርዕር ሰው ሲታወስ!
ባሕር ዳር ፡ ጥር 30/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሙሉ ስዓት ደራሲ፣ የተባ ብዕረኛ፣ ተወዳጅ ጋዜጠኛ፣ ብርቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የድምፅ አልባዎች ድምፅ፣ የነበረበትን ዘመን በብዙው የቀደመ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡
የነገስታት ኀይል የማያስፈራው፣ ጥቅምና ድለላ የማያማልለው፣ ላመነበት እና እውነት ነው ላለው ሁሉ እንደምሰሶ የበረታ፣ ሀገር ወዳድ እና ትሁት እንደነበር ይነገርለታል፤ እውቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ እና ጋዜጠኛ፡፡
በቀድሞ አጠራሩ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት አቸፈር ወረዳ ኮረንች በዓታ አካባቢ ሰኔ 25/1933 ዓ.ም አንድ ብላቴና ይችን ምድር በእንግድነት ተቀላቀለ፡፡ አፈር ገፊ እንጂ መሰናክሎችን ሁሉ አልፎ፣ ውጣ ውረዶችን ሁሉ ተሻግሮ እና ችግሮችን ሁሉ ተቋቁሞ በሌላ መስክ የወገኖቹ ህመም የሚያመው ልጅ ይሆናል ብሎ ያሰበ ባይኖርም መንፈሳዊንም ዓለማዊንም ትምህርት እንዲማር ተደረገ፡፡ ይስማላ ጊዮርጊስ ከሊቁ የኔታ ገሰሰ ዘንድ ቅኔን በአጭር ጊዜ ተምሮ በዙሪያው የነበሩትን ሁሉ ያስደመመው መረዋ ድምፁን ተፈጥሮ ለዜማ እንደለገሰችውም ይነገርልት ነበር፡፡
‹‹እንደወገል የሰው ልጅ ለአንድ ሙያ አልተፈጠረም›› ብሎ የሚያምነው ሁለገቡ የጥበብ ሰው የባህል መድኃኒት ቀማሚ፣ ትምህርት እና አዲስ ነገርን ናፋቂ፣ የመፅሃፍ ትል እና አንብቦ አይጠግቤ ለመሆኑ የኋለኛው ዘመን ስራዎቹ ህያው ምስክሮች ናቸው አቤ ጉበኛ፡፡ ይስማላ ጊዮርጊስ ከየኔታ ገሰሰ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርቱን በብቃት ያጠናቀቀው ሩቅ አሳቢ ለዘመናዊ ትምህርት ህንዶች በሚያስተምሩባት ዳንግላ ደርሶ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት በዚያው ተከታተለ፡፡
ወደ አዲስ አበባ አቅንተውም ቀሪውን የዘመናዊ ትምህርት በተለይም ደግሞ የእንግሊዝኛ ቋንቋን በአግባቡ መማሩ ይነገራል፡፡ በስራው ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በማስታዎቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ያገለገለው ጋዜጠኛ እና ደራሲ አቤ ጉበኛ ብዙም ሳይቆይ ግን የመንግስት ሥራውን አቋርጦ ወደሙሉ ጊዜ የድርሰት ሙያ ገባ፡፡
‹‹ከመቅሰፍት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት›› በሚል የግጥም መድበል አንድ ብሎም የድርሰቱን ዓለም ተቀላቀለ፡፡ ከቂመኛው ባህታዊ እስከ የሮም አወዳደቅ፣ ከፓትሪስ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት እስከ የዓመፅ ኑዛዜ፣ ከአልወለድም እስከ የፍጡራን ኑሮ፣ ከራሄል እምባ እስከ ከልታማዋ እህቴ፣ ከሐሜት ሱሰኞች እስከ አንድ ለእናቱ፣ ከመስኮት እስከ እድል ነው በደል፣ ከረገፉ አበቦች እስከ የህይዎት ትርጓሜዎች ከ25 በላይ መፅሐፍትን ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡
ሁለገቡ የጥበብ ሰው አቤ ጉበኛ አጭር እና ረጂም ልቦለዶችን፣ ተውኔቶችን እና የግጥም መድበሎችን ከመስራቱም በላይ ሁለት የእንግሊዝኛ መፅሐፍትንም ለህትመት አብቅቷል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አበረ አዳሙ የአቤ ሥራዎች በሀገር ፍቅር ላይ የሚያተኩሩ፣ ጭቆናን የሚቃወሙ፣ ባህላዊ ስሪቶቻችን አይተው የሚተቹ፣ ስለአንድነት እና ፍትሕ፣ ስለመልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ፣ ስለሰብዓዊ ክብር እና የህግ የበላይነት የሚሞግቱ ነበሩ ይላሉ፡፡
ጋዜጠኞችን ሃሰተኞች፣ ሐኪሞችን አላዋቂዎች፣ ባለሃብቱን በመታበይ፣ መኳንንቱን በትዕቢት እና ወታደሩን በጉልበት የሚነቅፉ እና የሚተቹ ሥራዎቻቸው ለድሃ ስለመቆማቸው ምስክሮች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
አቢዮተኛው የብዕር ሰው በንጉሰ ነገስቱ ዘመን የደብረ ብርሃን አውራጃ ገዥ እንዲሆኑ ሹመት ተሰጥቷቸው ነበር ያሉን የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንቱ አበረ አዳሙ ነገር ግን ይላሉ ‹‹ይህን መከረኛ ህዝብ እናንተ ስትገርፉት እንኳን ምን ያክል ደሜ እንደሚፈላ ቢያውቁት ይህን አይመኙልኝም ነበር›› በማለት አቤ ሹመቱን ውድቅ እንዳደረጉት ነግረውናል፡፡
የታህሳስ ግርግር በተነሳበት ወቅትም የሮም አወዳደቅ በሚለው መፅሃፍህ ምልኪ ተናግረሃል፤ ወጣቱንም አነሳስተሃል በሚል ለእስር ተዳርገው ነበር ይባላል፡፡
በተደጋጋሚ ‹‹ዓለምን የቸገራት የበጎ ሰዎች ማነስ ነው›› የሚሉት አቤ ማህተመ ጋንዲን፣ አብርሃም ሊንከንን፣ ፓትሪስ ሉሙምባ እና መሰል መልካም ሰዎች መገደላቸውን እያነሱ ‹‹ዓለም የገዳዮች ናት›› ብለው እስከመሞገት ደርሰው ነበር፡፡ በመጨረሻም ልክ የዛሬ 42 ዓመት ደራሲ አቤ በወቅቱ የስዓት እላፊ በታወጀባት አዲስ አበባ በሌሊት ሲንቀሳቀሱ በጥይት ተመትተው ጥር 30/1972 ዓ.ም ህይዎታቸው ዓለፈ፡፡ እኛም እውን ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ‹‹የገነት በሮች ይከፈቱልህ!›› ስንል እረፍተ ስጋቸውን ዘከርነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ