❝ዜጎች ከፋፋይ ከሆኑ ሐሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል❞ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

0
74

ጥር 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዜጎች ከፋፋይ ከሆኑ ሐሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማእከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማእከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ባለፉት ወራት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በጋራ ተሰልፈው ወረራውን መቀልበስ መቻላቸውን አንስተው፤ “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ የተነሳው የሽብር ቡድን በመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ዘመቻ ክፉኛ ተመትቶ ከወረራቸው አካባቢዎች መውጣቱን ተናግረዋል።

የጠላት አከርካሪ የተመታው በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እንደመሆኑ መጠን ድሉ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያመጡት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የተገኘውን ድል ለቀጣይ ሰላም እና ልማት እንዲሁም ሀገር ግንባታ መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በየደረጃው ያለ አመራር ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከሕግ ማስከበር እስከ ኅልውና ዘመቻው የታየውን ተናቦና ተቀናጅቶ የመሥራት አቅም ለመልሶ ግንባታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት የተገኘውን ድል ከምንም ጊዜ በላይ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው የውይይቱ ዓላማም ድሎቻችንን ተጠቅመን ሀገራችንን እንዴት በጋራ እናልማ ይሚል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶች ሳይገድባቸው ለአንዲት ኢትዮጵያ በጋራ መስዋእትነት በመክፈል በብዝኃነት ውስጥ አንድነታቸው የጠነከረ መሆኑን ማሳየታቸው በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል።

ይህን የተፈጠረውን አቅም ከድል በኋላ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ሥራ ማዋል የኹሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል የሚል ሐሳብ መነሳቱንም አብራርተዋል።

ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዴት እንገንባ፣ የተገኘውን የአመራር ቁርጠኝነት እንዴት እናስቀጥል፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጠንካራ የሕዝብና የመንግሥትን ግንኙነት እንዴት ይጠናከር የሚሉት የቀጣይ ሥራዎች ተብለው የተለዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመንግሥትም ኾነ በግል ቁጠባን መሰረት ያደረገ የአኗኗር ዘይቤ መከተል፣ የድኅረ ጦርነት ኢኮኖሚ መገንባት እና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ሥራዎችን ኹሉም በኃላፊነት ወስዶ መሥራት እንዳለበት በውይይቱ ተነስቷል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት የማይመቻቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ አንድ ሲሆኑ የማይወዱ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያ የውይይቱን ዓላማ ወዳልተገባ መንገድ በመተርጎም ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያን መገንባትና ማጠናከር የውይይቱ ዓላማ ኾኖ ሳለ በውይይቱ ያልተዘጋጀ ሰነድ አስመስለው በማዘጋጀት ላልተገባ የፖለቲካ ዓላማ እየተጠቀሙ መሆኑን አብራርተዋል።

በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን አንድነት ጠላቶች በሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ለማፍረስ ያዘጋጁት ሴራ በመሆኑ ዜጎች ከፋፋይ ከሆኑ ሐሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከሚከፋፍሉን ሐሳቦች በላይ መሆናችንን ማሳየት ይገባልም ነው ያሉት።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/