❝ከአፍሪካ ጋር ያለንን ትብብር በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ እንዲያድግ እንሠራለን❞ ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን

0
106

ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከአፍሪካ ጋር ያለን ትብብር በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ እንዲያድግ እንሠራለን ሲሉ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አስታወቁ።
ሦስተኛው የቱርክ- አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በቱርክ ኢስታንቡል በመካሄድ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ቱርክ እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ አካሄድ መቃኘቷን አስታውሰዋል። ይህም ከአፍሪካ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ከአፍሪካ ጋር የሚኖረንንም ግንኙነት “በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ እንዲያድግ እንሠራለን፣ ትስስሩ ኹሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንብት እንዲሆን ነው የምንሠራው” ነው ያሉት።

“አህጉሯን በሚጎዳ፣ ተገቢ ያልሆነና የግል ተጠቃሚነትን ብቻ የሚከተል አካሄድን ኹሌም ውድቅ በማድረግ ነው ከአፍሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት የምናሳድገው” ሲሉም ገልጸዋል።
ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ላላት ወዳጅነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነትም ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በጋራ ለመሥራት ያካሄደችውን ስምምነት ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በ3ኛው የቱርክ-አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።