❝አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ሀገር ሊያሳጣን፣ አንድነታችንን ሊያናጋ፣ ነፃነታችንን ሊገፍ፤ ጥሪታችንን ሊዘርፍ እና በዓለም የገነነውን ስማችንን ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳ ኃይል በመሆኑ ማጥፋት ምርጫ የሌለው ተግባር ነው❞ አቶ ዮሐንስ ቧያለው

0
205

❝አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ሀገር ሊያሳጣን፣ አንድነታችንን ሊያናጋ፣ ነፃነታችንን ሊገፍ፤ ጥሪታችንን ሊዘርፍ እና በዓለም የገነነውን ስማችንን ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳ ኃይል በመሆኑ ማጥፋት ምርጫ የሌለው ተግባር ነው❞ አቶ ዮሐንስ ቧያለው

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል እኩይ ተግባሩን ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል።

እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ከምሁራን በሚጠበቁ ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል።
ከእንጅባራ ዩኒቨርስቲ በውይይቱ የተሳተፉት ወይዘሮ ጥሩዬ አብዴ የህልውና ዘመቻው የመኖር ያለመኖር በመሆኑ ሁሉም ሰው መሳተፍ አለበት፤ እኔም የዘመቻው አካል ነኝ ብለዋል፡፡ ዘመቻው ለአንድ አካል ብቻ የተተወ ሳይሆን ሴት ወንድ፣ የተማረ ያልተማረ ሳይል ሁሉም የሚሰለፍበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ጥሩዬ ❝ሁሉም ሰው እኔ ምን ብሠራ ዘመቻው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ሀገር ወደ ልማት ትመለሳለች የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለበት❞ ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ኃይል በሚነዛው ወሬ መፈታት እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ጥሩዬ እንዳሉት ሴቶች፣ ሕጻናት እና አረጋውያን ረሀብን፣ ጥምን፣ እርዛትን እያስተናገዱ ነው፤ ይህንን አሸባሪ ኃይል ለመቅበር ለአንድ ዓላማ መተባበር ምርጫ ውስጥ ልናስገባው አይገባም ነው ያሉት።

❝ሴቶች የጦርነቱ አንቀሳቃሽ ኀይል ሊሆኑ ይገባል፤ የጣይቱን ታሪክ በመድገም ሽህ ጣይቱዎች ሊፈጠሩ ይገባል❞ ብለዋል።

የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ መምህር እውነቱ አማረ ዘመቻውን እንደሚቀላቀሉ ገልጸዋል፡፡ አንድነታችንን በማጠናከር ጠላትን መቅበር አለብን ነው ያሉት።

የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶክተር) እንዳሉት ምሁራን የህልውና ዘመቻውን በበላይነት ከመምራት ባሻገር አዳዲስ ሐሳቦች በማፍለቅ እና በመተግበር የጦርነቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ለህልውና ዘመቻው የሀብት አሰባሰብ ሥርዓቱ፣ የሰው ኀይል አጠቃቀም ሁኔታው ምን እንደሚመስል መለየት እና መተንተን ከምሁራን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

❝ትናንትን ለዛሬ ሥራችን መነሻ ለማድረግ መጠቀም ይገባል፤ ለነገ ዛሬን መነሻ ማድረግ እና አንድ ብሎ መጀመር ይገባል❞ ነው ያሉት፡፡

ምሁራን ሽብርተኛውን የትህነግ ወራሪ ኀይል ለመደምሰስ እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ እንደሚደግፉ እና በግንባር እንደሚፋለሙ ገልጸዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት በህልውና ዘመቻ ማስተባበሪያ የሕዝብ ንቅናቄ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በአማራ እና በአፋር ክልል ሕዝብ ላይ ጥቃት እያደረሰ ያለውን ሽብርተኛ ኃይል ለመደምሰስ እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ የምሁራን ድርሻ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ከመዘናጋት፣ የጠላትን አቅም አሳንሶ ከማየት ወጥቶ የጠላትን አሰላለፍ በመረዳት ጠላትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ዳግም በማያንሰራራበት ደረጃ ለማድረስ መሥራት እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

አቶ ዮሐንስ “ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ሀገር ሊያሳጣን፣ አንድነታችንን ሊያናጋ፣ ነፃነታችንን ሊገፍ ጥሪታችንን ሊዘርፍ እና በዓለም የገነነውን ስማችንን ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳ ኃይል በመሆኑ ማጥፋት ምርጫ የሌለው ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

“ጠላት ኢትዮጵያን ከፋሽስት ኢጣሊያ በላይ ይጠላታል” ያሉት አቶ ዮሐንስ ይህንን ኃይል ለመደምሰስ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ እድሜው የፈቀደለት ሁሉ እንዲሰለፍ መሥራት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ሕዝባዊ ማዕበሉ ማቀላቀል፣ ደጀኑ ሕዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በአንድነት ጠላትን ለመደምሰስ መሥራት ከምሁራን የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ