ደሴ: ጥቅምት 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ኃይል በፈጸመው ወረራ ንጹሐንን ገድሏል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ የግልና የመንግሥት ንብረት ተዘርፏል፤ ወድሟል። አሸባሪው ኃይል እየፈጸመ ያለውን ግፍ አሁንም ቀጥሎበታል።
የደሴና የአካባቢው ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ጋር በመሆን አሸባሪውን የትህነግ ኃይል ለመደምሰስ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው የትህነግ ኃይል በአማራ ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍ እንዲያበቃ ወደ ግንባር በመዝመት ወራሪው ኃይልን ባለበት ለመቅበር በፍፁም ቁርጠኝነትና ወኔ ወደ ግንባር ዘምተዋል።
ወጣት ጌታቸው ሳህሉ የግንባር ስምሪቶችን በመቀበል ወጣቶች ወደ ጦር ግንባር ወርደው መከላከያ ሠራዊትን፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ተቀላቅለው ወራሪውን ቡድን ለመቅበር እንደዘመቱ ተናግሯል።
❝በአባቶቻችን ደም እና አጥንት የተገነባች ሀገራችንን ለወራሪ ጠላት አሳልፈን አንሰጥም❞ ነው ያለው።
ወጣት አሊ አህመድ ጠላትን ለመደምሰስ ወደ ግንባር መዝመቱን ገልጿል።
“የጠላትን የጥፋት ሴራ እናመክናለን፤ ሀገራችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ብለን ወጣቶች በመሰባሰብ ወደ ግንባር ዘምተናል” ያለው ወጣት አሊ ከመከላከያና ከልዩ ኃይል ጋር በመሆን አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገብ እንደሚያፀዱም ገልጿል።
ሌላው ወጣት ተረፈ አልብሴ በበኩሉ የወራሪው ትህነግ ግፍን እንዳየ ገልጾ ሌላ ተጨማሪ ግፍ እንዳይፈፀም ከአካባቢው ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን ባለበት ለመፋለም መዝመቱን ተናግሯል።
የደሴ ከተማ ወጣት ሰርጎገቦችን በመቆጣጠር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቁርጠኝት ሲሠሩ መመልከቱን የገለፀው ተረፈ ከመከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ጠላትን ለመቅጣት ከደሴና ከአካባቢው ወጣቶች ጋር አብሮ ወደ ግንባር መዝመቱን ገልጿል።
ዘጋቢ:- ግርማ ሙሉጌታ – ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ