❝በአሸባሪው ቡድን የወደሙ ሀብቶችን መልሶ በመገንባት ሕዝቡ ለወራሪ ቡድኑ የማይበገር መሆኑን ማሳየት አለበት፤ ለዚህም ሊዘጋጅ ይገባል❞ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

99

ደሴ: ታኅሣሥ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በደሴ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም በአሸባሪው እና ወራሪው የትግራይ ቡድን የወደመውን ሀብት መልሶ ለማቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች፣ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ተቀላቅለው ሀገርን መታደግ እንዳለባቸው፣ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ፣ የተጀመሩ ልማቶች እንዲቀጥሉ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል።
አሸባሪ እና ወራሪው የትግራይ ቡድን ከፈጸማቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ባለፈ የግልና የመንግሥት ሃብቶችን ዘርፏል፤ አውድሟል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝቡ ተደራጅቶ ጠላትን ሊፋለም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወጣቶችም መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ወራሪው ቡድን ለዘመናት ያዳከመውን የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህ ሲሆን መንግሥትም ሕዝብን የመጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ያግዘዋል ብለዋል።
ወራሪው ቡድን በወገን ጥምር ጦር እርምጃ ተወስዶበት በርካታ አካባቢዎች ነጻ ወጥተዋል ያሉት ርእስ መሥተዳድሩ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሥራ ጀምረዋል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮም አገልግሎት በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋል፤ ለዚህም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡም በኹሉም አካባቢዎች ሰላምን በማስጠበቅ ለጸጥታ አካላት ተባባሪ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ሕዝቡም በቀጣይ የተሻለ የጤና ተቋም፣ ትምህርት ቤት እና ፋብሪካዎችን በመሥራት ለወራሪ ቡድን የማይበገር መሆኑን ማሳየት አለበት፤ ለዚህም ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል። የደሴና የኮምቦልቻ ጉዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳት ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
መሪዎችም ከኅብረተሰቡ ጋር እየተወያዩ ይሠራሉ፤ የወደመውን ንብረት ለመተካት የሀብት አሰባሰብ ሥራም ይሠራል፤ በጦርነቱ ምክንያት ዕለታዊ ምግብ ለሚቸግራቸው ወገኖችም ድጋፍ ይደረጋል፤ ተፈናቃዮችም የትራንስፖርት አግልግሎት በነጻ የተመቻቸ መሆኑን አውቀው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በፍጥነት ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ በመምጣት የወደመውንና የተዘረፈውን ሀብት በመመልከት እና ለቀጣይ መፍትሔ ከነዋሪዎች ጋር መወያየቱ የሚመሰገን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። በጠላት የወደመውን ንብረት ለመተካት ሕዝቡ በትጋት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ያጋጠመንን ችግር በጋራ እንሻገረዋለን ነው ያሉት።
በርካታ ወጣቶች ከወገን ጦር ጋር በመሆን ጠላትን ድባቅ በመምታት ከፍተኛ ጀብድ መፈጸማቸውን የገለጹት ነዋሪዎች በቀጣይም ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ለጠላት የማይደፈር አካባቢ ለመፍጠር በቁጭት መነሳታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦አዳሙ ሽባባው-ከደሴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation