❝በአማራ ምድር ላይ ድግስ የበላችሁ፣ ጀግናው አስጠንስሷል ዳግም ሊጠራችሁ❞

0
193
ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመናትን በቀደመ ባሕልና ሥርዓት የሚኖር፣ በደጋ በቆላው፣ መሬቱ ነጭና ጥቁር የሚያዘምር፣ ቋጥኝ የሚያክል የጤፍ ክምር የሚከምር፣ ለአራሹ ጮማ ጠላ፣ ጠጅና ፍርዱንስ፣ ለበሬው ገብስ የሚያቀርብ፡፡ ጠላቶች የሚፈሩት፣ በድምጹ የሚሸበሩለት፣ በግርማው የሚፈረጥጡለት፣ ወዳጆች የሚመኩበት፣ የሚኮሩበት፡፡ ለአሸናፊነት የተፈጠረ፣ ዝናው በዓለም ዙሪያ የተነገረ፣ በጀግንነቱ ምድሩን ያስከበረ፣ የበደል ዘመንን ያስቀረ፣ የጠላትን ክንድ የሰበረ፣ የበደለኞችን ሐውልት ያፈረሰ፣ አብዮታቸውን የገረሰሰ፣ ፍትሕን የመለሰ ሕዝብ፡፡
ተገፍቶ የማይወድቅ፣ ከክብሩ የማይነቃነቅ፣ ታሪኩ የተለቀ፣ እሴቱ የረቀቀ፣ ዝናው የደመቀ፣ ጀግንነቱ የታወቀ ነው፡፡ ሲወድ አፈር ስሆን እያለ የሚያጎርስ፣ ሲጠላ ተመልከት ብሎ አንገት የሚበጥስ፣ በወንዝ ማዶ የሚመለስ፣ አፈር የሚያለብስ፣ ክብር የሚያስመልስ ነው -አማራ፡፡
አማራ ጀግና ነው ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ ድንቅ ነው በታሪኩ ጉድፍ ያልተገኘበት፣ ጠቢብ ነው ደንጋይ እንደ አሽከር የታዘዘለት፣ ሩህሩህ ነው የደከመ የሚያርፍበት፣ የተቸገረ የሚበላበት፣ የተጠማ የሚጠጣበት፣ ተኳሽ ነው መሳት ብሎ የማይታወቅበት፣ ገትሮ ያርሳል፣ ተደላድሎ ያፍሳል፣ ጎተራውን በነጭና በጥቁር ይሞላል፡፡
በሰንደቁ ከማለ፣ አያሻኝም ካለ፣ መውዜሩን ከወለወለ፣ ሀገሬን አትንኳት ብሎ ከሸለለ በኋላ የሚያቆመው ማሸነፍ፣ ጠላትን መቅሰፍ፣ ስምን ከፍ አድርጎ መጻፍ ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለአማራ ዘውዱ ናት የሚነግሥባት፣ ዙፋኑ ናት በክብር የሚቀመጥባት፣ ካባው ናት የሚያጌጥባት፣ ጥላው ናት የሚያርፍባት፣ ቃል ኪዳኑ ናት የሚያከብራት፣ የማይሽራት፣ ነብሱ ናት የሚኖርባት፣ የሚኖርላት፣ ብሌኑ ናት የሚሳሳላት፣ የሚጠብቃት፣ ክብሩ ናት የሚከበርባት፣ አልማዙ ናት የሚደምቅባት፣ የክብር ልብሱ ናት የሚያጌጥባት፣ ስጋና ደሙ ናት የማይለያት፣ ከምንም በላይ ናት ከኹሉ የሚያስቀድማት፣ በምንም የማይለውጣት፣ ከምንም ጋር የማያወዳድራት ከኹሉም አስበልጦ የሚወዳት፣ የሚኖርላት፣ የሚሞትላት፣ የሚስከብራት፣ ቤቱ ናት ወግ ማዕረግ የሚያይባት፡፡
ጠላቶች ኢትዮጵያን ሊነኩ በተነሱ ቁጥር አማራ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ኾኖ ጦር ሰብቆ፣ ትጥቁን አጥብቆ ወደ ዘመቻ እየገሰገሰ፣ ጠላቱን እየደመሰሰ፣ ሀገርን ከነክብሯ እና ከነ ድንበሯ ዛሬ ላይ ያደረሰ ሕዝብ ነው፡፡
አማራ በጀግንነቱ ጠላት በአጭር ያስቀራል፣ በብልሃቱ መልካም ሥርዓት ይሠራል፣ በጥበቡ አብያተ መንግሥት ይገነባል፣ መቅደስ ያንጻል፡፡
አማራ ጀግንነትና ብልሃት፣ ሩህሩህነትና አሸናፊነት፣ አርቆ አሳቢነትና አይደፈሬነት በጋራ ያሉት ሕዝብ ነው፡፡ የአማራ ጀግንነት ምስጢሩ አልገባ ቢላቸው፣ አይደፈሬነቱ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ፈለጉ አላላውስ ያላቸው፣ የግፍ እርምጃቸውን የገታባቸው፣ የክፋት ክንዳቸውን የቀነጠሰባቸው ጠላቶች በቤተ መንግሥቶቻቸው እንዴት እናሸንፈው፣ እንዴትስ እናጥፋው ሲሉ ዶልተውበታል፣ ረቂቅ አርቅቀውበታል፣ ወታደር አዝምተውበታል፣ የተሳሳተ ታሪክ አሠርተውበታል፡፡ ዳሩ መንገዳቸው ኹሉ ከአማራ ጥበብና ጀግንነት በታች ነውና፣ ምስጢሩና ክብሩ ረቂቅ ኾነና ያዘመቱት ወታደር ሞቶ አለቀ፣ የሠሩት ኹሉ እንዳልነበር ኾነ፡፡
ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ረግጠው የመጡት ኹሉ በሀፍረት ተመለሱ፣ ለተከበው ሕዝብ እጅ ነሱ፡፡ በአሻገር ሲያዩ የነበሩ ኹሉ ጀግንነቱን አወደሱ፡፡ እርሱም ከታሪክ ላይ ታሪክ ጨመረ፣ በአሸናፊነት ዘመረ፡፡ አማራ የውጭ ጠላት ሲያርፍለት የውስጥ ጠላቶችም ይነሱበታል፡፡ እንዳያርፍ ይነካኩታል፣ ከውቅያኖስ የጠለቀውን ትዕግስቱን ይፈታተኑታል፣ ከተራራ የገዘፈው ጀግንነቱን ይነካኩታል፤ እርሱም ታግሶ ይነሳል፣ ነፍጡን ያነሳል፣ አጥፍቶ ይመለሳል፡፡ አማራ በሰው ላይ ግፍ አይሰራም፣ ገፍተው ከወጉት፣ ለግፍ ከጋበዙት ግን ውጊያ እንዴት እንደሆነ ያሳያል፤ አማራን ማጥፋት ዓባይን በማንኪያ ጨልፎ እንደ መጨረስ፣ የራስ ደጀን ተራራን ገፍትሮ እንደማፍረስ፣ ያለፈን ዘመን እንደመመለስ፣ ሰማይን እንደመዳበስ፣ የምድር አሸዋን የሰማይ ከዋክብትን ቆጥሮ እንደመጨረስ ይቆጠራል፡፡ ችለው አያጠፉትም፣ ኾኖላቸው አይገፉትም፣ በጀግንነት፣ በጽናት፣ በእሴት በኹሉም ነገር ይበልጣቸዋልና፡፡ ጠላቶቹ ኹሉ ከእርሱ በታች ናቸው፡፡ እምቢ ለነጻነት፣ እምቢ ለማንነት ብሎ ከተነሳ የሚመልሰው ከቶም የለም፡፡
አማራ አትንኩኝ አልነካችሁም ይላል፣ ደፍረው ከነኩት የጥይት እሩምታ፣ የሰው ጋጋታ፣ የጠላት ድንፋታ አያስቆመውም፡፡ እየመከተ፣ እያነከተ ወደፊት ብቻ ይገሰግሳል፡፡
አማራ ዛሬ ላይ ቀደም ሲል የተነሱት የውጭ ጠላቶች መነሻ በሰጡት እኩይ ጠላት እየተገፋ ነው፡፡ ሀገር ያቆዬውን፣ ታሪክ የሠራውን፣ ወገን ያስከበረው ሕዝብ እየወጉት፣ እየገደሉት፣ እያፈናቀሉት ነው፣ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኃይል በአማራ ሕዝብ በደል እየፈጸመበት ይገኛል፡፡
የአማራ ሕዝብ የወለዳቸው በጀግንነት ያሳደጋቸው፣ ፋኖዎች ሚሊሻዎች፣ ልዩ ኃይሉና ወጣቱ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን እየመከቱት፣ የደመሰሱት፣ ክንዳቸውን እያቀመሱት ነው፡፡
በሕልውና ዘመቻው ጠላትን ቀብሮ ደስታን ለማብሰር ብርድ ሳይበግራቸው፣ ቁር ሳያስቆማቸው እየታገሉት ነው፡፡ በአማራ ላይ ያልተዶለተ ነገር የለም፣ ያልተዘጋጀ ማጥፊያም አልነበረም ዳሩ በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም፡፡
አማራ አሁን ላይ ኹሉም ወደ ግንባር በሚለው የሕልውና ዘመቻ ወደፊት እየገሰገሰ ነው፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ሀብት ያለው በሃብቱ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ ቀሪው ደግሞ በጸሎቱ ኹሉም ግንባር ላይ ነው፡፡ አማራ በኢትጵያ የሚመጣውን መከራ ኹሉ የሚሸከም ሕዝብ ነው፣ ሀገር ለመውረር ጠላት በመጣ ቁጥር መከራን በመቀበል ሀገር ይታደጋል፣ ዛሬም ይሄው ነው እየሆነ ያለው፡፡
ʺበአማራ ምድር ላይ ድግስ የበላችሁ
ጀግናው አስጠንስሷል ዳግም ሊጠራችሁ” እንደተባለ በአማራ ምድር ላይ ጠላት ተመትቶ ወድቅ ድግስ የበላችሁ፣ በተሠራው ጀብዱ የተደሰታችሁ፣ በአሸናፊነቱ የኮራችሁ፣ በአይደፈሬነቱ የጨፈራችሁ ኹሉ ጀግናው ዳግም አስጠንስሷል፣ ከድግሱ ሊያበላችሁ፣ ከመጠጡ ሊያጠጣችሁ፣ አሁን ላይ ባለው ጠላት የመጨረሻው ድግስ፣ የመጨረሻው ጥንስስ ተጠንስሷል፡፡ ጥንስስ ጠንሳሾቹ ጀግኖች ድግሱን እያበሳሰሉ፣ የሠርጉን ቀን እያቀረቡት ነው፡፡ ታዲያ በደስታቸው ለመደሰት የሚሻ ኹሉ ለጥንስሱ መብሰል፣ ለድግሱ መድረስ የሚያስፈልጋቸውን ኹሉ በማገዝ ይተባበር፡፡
ከአሁን በፊት ከአማራ እሸት የበላችሁ፣ ከጠጁ የቀመሳችሁ፣ ከጠላው የደረሳችሁ፣ ከወተቱ የተጎነጫችሁ፣ ጤፍ እንጀራውን የጎረሳችሁ፣ ከፍቅሩ የተጋራችሁ ኹሉ ዛሬም ሌላ ድግሥ ደግሷል፡፡ ሊጠራችሁ ጠንስሷል፣ ሊያስጨፈር፣ አንበሳ ገዳይ ሊያዘመር ተዘጋጅቷል፡፡ አሽንፎ መዘመር፣ ልጅ ወልዶ መዳር፣ ጠላት አሸንፎ መክበር፣ ማስከበር መከበር መገለጫው ነው፡፡ ሂድ አንተ ጀግና ጥንስሱ ወደ ተጠነሰሰበት፣ ሂድ አንተ ቆራጥ፣ ድግስ ወደ አለበት፣ ጠላት ወደሚቀበርበት፣ የወገን አንገት ወደሚቃናበት፣ ክብር ወደሚመለስበት፣ ነጻነት ወደሚጸናበት፣ በድልህ እናቶች ወደሚስቁበት፣ የጠላት ደጋፊዎች ኹሉ ወደሚያፍሩበት፣ ከዋሻ ስር ወደ ሚደበቁበት፣ ስምህ ወደሚከብርበት፣ ዝናህ ወደሚናኝበት፣ ሀገር ወደሚከብርበት፡፡
አማራ የሚለውን ስምህ አንገበህ፣ ኢትዮጵያ የምትለውን ክብርህን አስቀድመህ፣ በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ በሰንደቅ ተማምለህ ገስግስ፣ ጠላትን መልስ፡፡ ከድግሱ የሚበሉት፣ በደስታህ የሚደሰቱት ቸኩለዋልና፡፡ የጠላትን አወዳደቅ ማየት ናፍቀዋልና፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ