❝መስቀል የብሩህ ተስፋ፣ የብርሃንና የድል ምልክት ነው ፤ ደመራም የአንድነት እና የሕብረት ተምሳሌት ነው❞ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

0
67

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ለመስቀል የደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።

እንኳን ለመስቀል የደመራ በዓል በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

የመስቀል በዓል ለሀገራችን ሕዝቦች ባህላዊ እሴት በመሆን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ተልዕኮው ባሻገር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባህላዊ ቅርስና ውርስ ነው። መስቀል የብሩህ ተስፋ፣ የብርሃንና የድል ምልክት ነው። ደመራም የአንድነት እና የሕብረት ተምሳሌት ነው።

በመሆኑም እንደ ሀገር የገጠሙን ችግሮች በጋራ ታግለን ለድል መብቃት የምንችለው በአንድነትና በትብብር መቆም ስንችል መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የጦርነት ታሪኮችን አሳልፋለች፡፡ የጦርነት ታሪኮች ግን በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቱን ለመበተን ከውስጥና ከውጭ በተነሱ ኃይሎች እንጂ በኢትዮጵያውያን ግፊት የተከሰቱ አልነበሩም።

በተለያዩ ወቅቶች የመጡብንን ወራሪ ኃይሎች ጀግኖች አባቶቻችን በወኔና በቆራጥነት በመመከት ሰላሟ የተረጋገጠና በማንም አይነት የውጭ ባዕድ እጅ ያልወደቀች ነጻ ሀገር አስረክበውናል፡፡ ነጻና ዳር ድንበሯ የተከበረን ታሪካዊት ሀገር ለዛሬው ትውልድ ለማውረስም የሕይወትና የአካል መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡

አያት ቅድመ አያቶቻችን በአንድነት ተሳስረው ጠላትን እየመከቱ ዛሬ የምንኮራበትን ታላቅ ሀገር እንዳወረሱን ሁሉ ዛሬም ጀግናው የወገን ጦር ከወራሪው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ጋር በፍጹም የሀገር ፍቅር ስሜት እየተፋለመ ይገኛል።

በመሆኑም አሸባሪው ሕወሓት በእብሪት የከፈተብንን ወረራ ቀልብሰን የሀገራችን እና የሕዝባችን ሰላምና ነጻነት ለማረጋገጥ በጽናት የምንታገልበት፣ ለወገን ጦር ደጀንነታችን በተግባር የምናሳይበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጀመርናቸው የልማት ሥራዎቻችን ያለምንም መስተጓጎል ለስኬት እንዲበቁ በጋራ ርብርብ የምናደርግበት ሊሆን ይገባል።

ስለሆነም የመስቀልን በዓል ስናከብር ለሀገርና ለሕዝብ ኅልውና ከጠላት ጋር እየተዋደቀ ለሚገኘው ለወገን ጦር በሁሉም ዘርፍ ደጀንነታችን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪ እያቀረብሁ፤ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና አንድነት እንዲሆን በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም እመኛለሁ።

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J