❝ለሠራዊቱ አባላት የተሰጠው የማዕረግ እድገትና ሽልማት በደጀንነት የተሰለፈው ሕዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ነው❞ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

187

ጥር 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊቱ አባላት የተሰጠው የማዕረግ እድገትና ሽልማት በደጀንነት የተሰለፈው ሕዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ጭምር መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

የሀገር ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ያልተገባ አሉባልታ የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ነው ያስጠነቀቁት፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የኅልውና አደጋ በመቀልበስ አኩሪ ገድል መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ የተገነባበት ሕዝባዊ መሰረትና ያለው ጠንካራ የአመራር ትስስር ሠራዊቱ ላስመዘገበው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው ያነሱት፡፡

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ መነሳቱ በሠራዊቱና ደጀን በኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኅልውና ለመጠበቅ በተካሄደው ውጊያ በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊቱ አባላት የተበረከተው የማዕረግ እድገት እና ሽልማት በቀጣይ ለሀገራቸው ፊት ለፊት የሚቆሙ ጀግኖችን በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ሽልማቱ የሠራዊቱ ብቻ ሳይኾን ከሠራዊቱ ጎን የተሰለፉ የክልል የጸጥታ ኃይሎችና ደጀኑ ሕዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡፡

አኹን ላይ ሠራዊቱ ራሱን ይበልጥ በማደራጀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅሙን በመገንባት የትኛውንም የኅልውና አደጋ መቀልበስ በሚያስችል ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሠራዊቱ ከሌሎች ጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ያስወጣበትን ብቃት የሠራዊቱ ዝግጁነት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ከወረራቸው አካባቢዎች የወጣው በሠራዊቱ ተቀጥቅጦና ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ገጥሞት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የሽብር ቡድኑ ሽንፈቱን በመሸፋፈን የትግራይ ሕዝብንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል እጅግ አሰልቺና የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን የትግራይ ሕዝብን አፍኖ ከፍተኛ በደል እያደረሰበትና እያሰቃየው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ “ማሸነፍ የምችለው በሕዝብ ማእበል ነው” በሚል የተሳሳተ አካሄድ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን በግድ ወደ ጦርነት በመማገድ ማስጨረሱ ደግሞ የቡድኑን ጭካኔ ያሳያል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ ቆምኩለት ለሚለው የትግራይ ሕዝብ ግድ እንደሌለው በተደጋጋሚ ማሳየቱንም ነው ያነሱት፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብራክ ክፋይና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻው ምሽግ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በዚህም ሠራዊቱን መደገፍ የሀገርን ኅልውና ማጽናት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ሠራዊቱ ላይ ያልተገባ አሉባልታ መንዛት ግን በሀገር ኅልውና ላይ አደጋ ለመጣል መሞከር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ሠራዊት ላይ ያልተገባ አሉባልታ የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ነው ያስጠነቀቁት፡፡

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️

#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️

#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️

#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/