❝ሁላችንም አንድ ኾነን የአፍሪካ አህጉርን የሚፈታተኑ ችግሮች ላይ መወያየትና መፍታት ተገቢ ነው❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

0
94

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በባሕር ዳር እየተካሄደ በሚገኘው የጣና ፎረም ላይ እንዳሉት በፎረሙ የአፍሪካን ውበትና ባሕል ማየት አስደሳች እንደሆነ ተናግረዋል።

❝ሁላችንም አንድ ኾነን የአፍሪካ አህጉርን የሚፈታተኑ ችግሮች ላይ መወያየትና መፍታት ተገቢ ነው❞ ብለዋል። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፈታት ይኖርበታልም ነው ያሉት።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ኾናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ የውኃ እጥረት እያጋጠማት በመኾኑ ይህን ለመታደግ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኀይል ልማት ላይ እየሠራች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በውኃ፣ በፀሐይ፣ በነፋስ የሚሠራ የኀይል ማመንጫ ልማት ላይ አተኩራ እሠራች ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ኢትዮጵያ የራሷን የኤሌክትሪክ ኀይል ፍላጎት በማሟላት ሌሎች ሀገራትንም ተጠቃሚ እያደረገች መኾኗንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በዝናብ ላይ የተመሠረተው ግብርና 30 በመቶው ምርት እያስገኘ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኽን ለማሻሻል ግብርናውን በማዘመን የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትን በስፋት በማከናወን ለሌሎች ሀገራትም እያስተዋወቀች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። የሀገሪቱ ዓላማ 20 ቢሊዮን ሀገር በቀል ችግሮችን ማልማት እንደኾነ ተናግረዋል። ነገር ግን ከእቅድ በላይ በመሥራት 25 ቢሊዮን ችግኞችን ማልማት እንደተቻለ ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥም 70 በመቶው መጽደቁን ነው የገለጹት።

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄው አንድ ሚሊዮን ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼