ፖሊስ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ያደረገውን ጸጥታ የማስከበር ሥራ በድኅረ ምርጫም አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

0
28

ፖሊስ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ያደረገውን ጸጥታ የማስከበር ሥራ በድኅረ ምርጫም አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በአማራ ክልል በሰላም ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡
በምርጫው ከወንጀል ስጋት ነጻ ሆኖ ሕዝብ ያመነበትን እንዲመርጥ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ምርጫው በአማራ ክልል ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር በሰላም
መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ከመምረጥ ባለፈ ሰላሙን በመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ፣ የጸጥታና የደኅንነት አካላት ላደረጉት አስተዋጽዖም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የክልሉ እና የፌደራል የጸጥታ መዋቅር በጋራ በመቀናጀት ከምርጫው ገለልተኛ በመሆን በሰላም እንዲጠናቀቅ አድርገዋልም ነው ያሉት፡፡
የጸጥታ ኃይሉ የሕዝብ ሰላምና ደኅነንት እንዲጠበቅ ሌት ከቀን ከመሥራት በላይ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት መክፈሉንም ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ በምርጫ ጣቢያ ላይ በነበሩ የፖሊስ ኃይሎች በተከፈተ ጥቃት የፖሊስ አባላት መስዋዕትነት ከፍለዋልም ብለዋል፡፡ በደረሰው ጥቃትም
አንድ የፖሊስ ኃይል ሕይወቱ ሲያልፍ አንዱ ደግሞ መቁሰሉንም አስታውቀዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያ ሥራ ላይ የነበሩ አባላት ለምርጫ የመጡ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ፍቱ
እንዳሏቸውና አንፈታም ብለው ተኩስ መክፈታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ጥቃቱን ካደረሱት ሁለት ሰዎች መሞታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ የጥቃቱን መነሻና ሂደት እያጣራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የፖሊስ አባላቱ ለሕዝብ ሰላም ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት ስማቸውን ሲያስጠራ ይኖራል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
ምርጫው መስዋዕትነት ተከፍሎበትም መካሄዱን አስታውቀዋል፡
የፖሊስ አባላቱ የከፈሉት መስዋዕትነት ትክክለኛ የሕዝብ ልጆች መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲል ሕይወቱን ላጣው የፖሊስ አባል ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የታዩ ጥቃቅን ክፍተቶችን
እየተከታተሉ እርምጃ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
የታዩ ክፍተቶችን በጋራ በማረምና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምስገና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የምርጫ ውጤት በሚመለከተው አካል እስኪገለጽ ድረስ የጸጥታ ኃይሉ የሕዝብን ሰላምና ደኅነነት የማስጠበቅ ሥራውን ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ ኃይል በሚሠራው ሥራ የክልሉ ሕዝብ ከክልልና ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር እስካሁን ያሳዬውን አጋርነት እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፖሊስና ሌላው የደኅነንት ኃይል ምርጫው ከወከባ ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርጓልም ብለዋል፡፡
የትኛውም አካል የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ ” ከዚያ ውጭ ግን ሕጋዊና ሕገወጥነትን አደበላልቆ ሀገር አተራምሳለሁ ብሎ ሌላ እንቅስቃሴ
ውስጥ የሚገባ ካለ በሕግ አግባብ አጥፊውን ከንጹሐን በመለዬት የማስተማር ሥራ ይሠራል” ነው ያሉት፡፡
ፖሊስ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ያሳዬውን ተግባርና ሕግ የማስከበሩ ሥራ ያለ ምንም ድርድር በቁርጠኝነት ይቀጥላል ብለዋል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here