“ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትህትና፣ እንግዳ አቀባበል፣ ባህልን እና እምነትን ማክበር እንደ ኢትዮጵያዊያን” ይባል ነበር- መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ

0
251
“ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትህትና፣ እንግዳ አቀባበል፣ ባህልን እና እምነትን ማክበር እንደ ኢትዮጵያዊያን” ይባል ነበር- መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት በፅናት ታግላለች፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር አንድነት እና እድገት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ወጣቶች በትምህርት እንዲጎለምሱ ነፃ የትምህርት ዕድል ትሰጥ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአውሮፓዊያንን የቅኝ ግዛት ስርዓት ቀድማ ከመታገሏም በላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል የአፓርታይድ ፖሊሲን በመቃዎም ቀዳሚዋ እና ፈር ቀዳጇ ሀገር ነበረች፡፡
የአድዋ ድል ለፀረ-ኮሎኒያሊዝም ትግል መጠናከር በር ከፋች ድልም ነበር፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል እንቅስቃሴ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረው ከዓድዋ ድል ማግስት ጀምሮ ነበር፡፡
የአውሮፓዊያኑ ቀኝ ገዥዎች የበርሊን ጉባኤ ግራ የተጋባው ከአድዋ ተራሮች የጀግንነት ውጊያ ውጤት በኋላ መሆኑን እነርሱም አይክዱም፡፡
በዓድዋ የድል ብስራት ዝማሬ የከሰመው የአውሮፓዊያኑ የበርሊን ጉባኤ ዓላማው በወቅቱ የገጠማቸውን ከፍተኛ የጥሬ እቃ እጥረት እና የገበያ ፍላጎትን ማርካት ነበር፡፡ ወረራው “የግዛት ማስፋፋት” የተሰኘ የዳቦ ስምም ወጣለት፡፡ በዚህ ጉባኤ አፍሪካ ለአውሮፓዊያኑ ቀኝ ገዥዎች የቅርጫ ስጋ ገፀ በረከት ሆና ቀረበች፡፡
በወቅቱ አፍሪካ እና ሕዝቦቿ በቅኝ ግዛት ፅልመት ተቀርቅረው ነበር፡፡ ጥቁሩ ንጉስ ምኒልክ በዓድዋ የለኮሰው የድል ብስራት ችቦ ግን አፍሪካን ከፅልመት ወደ ብርሃን አሸጋገራት፡፡ ረመጡ ግን አውሮፓዊያን ወራሪዎችን ክፉኛ ለበለባቸው፡፡ እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ስሌት ከ1884 እስከ 1885 “ነፃ የምትባል አፍሪካ አትኖርም” ነበር ያሉት የበርሊን ጉባኤ ተሳታፊዎች፡፡
አስቀድመው ኢትዮጵያን በአነስተኛ ወረራዎች ለማዳከም ልምምድ ላይ የነበሩት ወራሪዎቹ በውጫሌው የስምምነት ውል አዘናግተው 1888 (እ.አ.አ) በጀኔራል ባራቴሪ የጦር መሪነት ሙሉ በሙሉ ለመውረር የካቲት 23 ከዓድዋ ተራሮች ግርጌ ከጥቁሩ መሪ ሠራዊት ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡
የበርሃው ንዳድ ሲቀንስ ፀሐይ ከአናት ወደ ግንባር ስታሽቆለቁል የማታ ማታም ድል ለተገፉት ሆነ፡፡ ከሊዝበን እስከ ሮም፣ ከፓሪስ እስከ ለንደን፣ ከበርሊን እስከ ማድሪድ ውጤቱ ለመላው አውሮፓ የሚታመን አልሆን አለ፡፡ የአድዋውን ጦርነት ውጤት የሰሙት ፋሽሽት አውሮፓዊያን ክፉኛ ቅስማቸው ተሰበረ፡፡
“ኢትዮጵያዊያን በተደረገው ውጊያ አሸነፉ፤ በእውነቱ በአንድ አውሮፓዊ ኀይል ላይ የአፍሪካዊ ታላቅ ድል” ተባለ፡፡
እስከአፍንጫው የታጠቀን፣ ሰልጥኛለሁ ብሎ የሚያስብን፣ ቅኝ መግዛት የ40 ቀን ዕድሉ ተደርጎ የሚታሰብለትን ወራሪን የሀገር ፍቅር ስሜት የናጠው ወዶገብ፣ ብረት ያልነካ ጀሌ እንደምንስ ማሸነፍ ተቻለው? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክ መምህር እና በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ዘመነወርቅ ዮሐንስ ጣሊያኖች ለገጠማቸው ሽንፈት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ግን የተሳሳተ ግምት እና መላምት መያዛቸው ነበር ብለዋል፡፡
አውሮፓዊያኑ ወራሪዎች በበርሊን በነበራቸው ጉባኤ አፍሪካን የሳሉበት መንገድ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ዋጋ ያስከፈላቸውም ነበር ነው ያሉት፡፡
ከጣሊያን ግልፅ ወረራ በፊት ኢትዮጵያኒዝምን የመታገያ መርሃቸው ያደረጉ የዓለም ጥቁሮች “ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትህትና፣ እንግዳ አቀባበል፣ ባህልን እና እምነትን ማክበር እንደ ኢትዮጵያዊያን” በሚል ያወጡትን ስድስት የመታገያ መርሆዎች ማየት እንኳን አልቻሉም ነበር ብለዋል፡፡
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንድን ሕዝብ እና ሀገር የመታገያ መርህ ሲያደርጉ ሊከተሉት የፈለጉት መርህ መኖሩን መገንዘብ ነበረባቸው ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያዊያን በራስ መተማመን፣ የዓላማ ፅናት፣ ሀገር ወዳድነት፣ የቆየ የሀገረ መንግሥት መስረታ ታሪክ እና ጠንካራ ግብረ ገብነት ያለው ሕዝብ መሆን ወራሪዎቹ እንደፈለጉት ገብተው እንዳይወጡ አድርጓቸዋል ብለዋል መምህር ዘመነወርቅ፡፡
ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ልዕልና እና ከፍታ ዛሬም ያንን ጠንካራ በራስ መተማመን መመለስ እና ትውልዱ ታሪኩን እንዲያውቅ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ፡- የኤርምያስ ጉልላት “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና ፓን አፍሪካኒዝም” መጽሐፍ
ዘጋበ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ