ፋሲል ከነማ የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቃል ተገባለት፡፡

0
604

ፋሲለ ከነማ እግር ኳስ ቡድንን ለማጠናከር የደጋፊ ማኅበሩ የገቢ ማሰባሰብና ሀብት ማፈላለግ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ፈረደ ለአብመድ እንደተናጋረው ቡድኑን ለማጠናከር ማኅበሩ በሀብት ማፈላግ ሥራ ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው፡፡

እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለጸ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድንን ለማጠናከር የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከሰሞኑ ቃል ገብቷል፤ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መካከል ደግሞ አቶ ወርቁ ዓይተነው ትናንት ከደጋፊ ማኅበሩና ከቡድኑ አባላት ጋር ተነጋግረው 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን በገንዘብ አቅሙ ተጠናክሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት ወደሚችልበት ደረጃ እንዲደርስ ደጋፊ ማኅበሩ የድጋፍ የመነሻ ሐሳቦችን (ፕሮፖዛል) ቀርጾ ለተቋማትና ግለሰቦች እየሰጠ መሆኑን የተናገረው ሊቀ መንበሩ ከተናጠል የድጋፍ ጥያቄው በተጨማሪ እንደ ጎዳና ላይ ሩጫ ያሉ የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶች መታቀዳቸውንም አስታውቋል፡፡

የጎዳና ላይ ሩጫው መቼና የት፣ በማን ስፖንሰር አድራጊነት እንደሚካሄድ ወደፊት እንደሚያስታውቁ የገለጸው አቶ ኃይለማርያም ሌሎችንም ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶችን በመፍጠር ፋሲል ከነማ እንዲጠናከር እንደሚሠሩ አመልክቷል፡፡

ፋሲል ከነማ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ የወንዶች እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ እየመራ ይገኛል፤ በውጤታማነቱ እንዲቀጥል ደግሞ የገንዘብ አቅሙን ማጎልበትና የተጫዋቾቹን በራስ መተማመን መገንባት፣ የስታዲዬሙን ደረጃ ማሳደግ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ከቡድኑ በተመጨማሪ የደጋፊ ማኅበሩ ጉልበት ሆኖ እየሠራ እንደሆነ ነው ሊቀ መንበሩ ያመለከተው፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

ፎቶ፡- ከፋሲል ከነማ ማኅበራዊ ገጽ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here