ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዎርጊስ የሚያደርጉት የዛሬው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

163
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐግብር ፋሲል ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ከቀኑ 9.00 ያደርጋሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ42 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ27 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ሲገጥመው አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊግ መሪነቱን ለማጠናከር በአንጻሩ ፋሲል ከነማ ደረጃውን ለማሻሻል የሚደረግ መሆኑ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐግብር ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊጉ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማና ሃዋሳ ከተማን ከምሽቱ 12.00 ላይ ያገናኛል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሦስት ጊዜ ተሸንፏል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። ሦስት ጊዜ አሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!