ፋሲል ከነማን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ዛሬ ለ11ኛ ጊዜ የሚያገናኘው የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ ይጠበቃል።

0
195

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ተከታዩ ፋሲል ከነማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይካሄዳል።

46 ነጥብ ያለው ፋሲል ከነማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከፈረሰኞቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ በማድረግ በዋንጫ ፉክክሩ እንዲቆይ ያደርገዋል።

ፕሪሚየር ሊጉን በ54 ነጥብ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ካሸነፈ ከፋሲል ከነማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 በማስፋት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይበልጥ ይቃረባል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ አንድም ሽንፈት ሳያስተናግድ በአስደናቂ ግስጋሴ ላይ ይገኛል።

በአንጻሩ በአሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ የሚመራው የአምናው የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አራት ጊዜ የተሸነፈ ሲሆን፤ ከሽንፈቱ መካከልም በ10ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር በዛሬ ተጋጣሚው 4 ለ 0 የተረታበት ጨዋታ ይገኝበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንደሆነ የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያመለክታል።

ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ አራት ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን፤በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በግንኙነታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 15 ፋሲል ከነማ ደግሞ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የፈረሰኞቹና የአፄዎቹ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአሁኑ ሰአት በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አዳማ ከተማና ሰበታ ከተማ ጨዋታቸውን እያደረጉ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አዲስ ተስፋዬ ባስቆጠረው ግብ አዳማ ከተማ 1 ለ 0 እየመራ ይገኛል።

ከቀኑ 7 ሰአት አርባ ምንጭ ከተማ ከወላይታ ዲቻ ይጫወታሉ።
ትናንት በተደረጉ የሊጉ መርሃ ግብሮች ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ ሃዋሳ ከነማን 3 ለ1 ሲያሸንፍ፤ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

ነገ በ25ኛ ሳምንት ከረፋዱ 4 ሰአት ባሕር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ከቀኑ 7 ሰአት ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሳምንቱ መጨረሻ መርሃ ግብር ከቀኑ 10 ሰአት መከላከያና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኛል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/