“ፋሲል ከነማን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

0
64
“ፋሲል ከነማን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ፋሲል ከነማ የአንድነት፣ የጥንካሬና ተስፋ ያለመቁረጥ ምልክት መኾኑን ገልጸዋል።
ከምስረታው ጀምሮ በተጓዘባቸው የውድድር ጊዜያት እየተሸነፈም ሆነ እያሸነፈ የቆየው ፋሲል አሁን ጠንክሮ በመሥራቱ ለድል በቅቷል። ለዚህም ለክለቡ አባላት፣ ለአስልጣኞች አባላትና ለደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ከፋሲል የውድድር ጉዞ እና የድል ብሥራት ኢትዮጵያውያን የሚቀስሙት ትምህርት እንዳለም ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የገለጹት።
ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ እና የአንድነት አቀንቃኝ መሆኑን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሉን ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል። በቅርቡም በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የቡድኑ ደጋፊዎች ግንባር ድረስ በመሄድ ድጋፍ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።
አቶ አገኘሁ እንዳሉት ፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያለበት ቡድን ነው። ነገር ግን በክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በባለሀብቶች ድጋፍ እንዲሁም መንግሥት በሚመድብለት አነስተኛ በጀት ችግሩን ተቋቁሞ ለውጤት መብቃቱን አመላክተዋል።
ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የውድድር መድረኮች ውጤታማ እንዲሆን ሕዝባዊ መሠረት ማስያዝ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ፋሲል ከነማ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ክለብ በመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚፈልቁ ስፖርተኞች ይሰለጥኑበታል ተብሎ የታሰበውና ጎንደር ላይ ለመገንባት ለታቀደው ግዙፍ የስፖርት አካዳሚ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል። የፌዴራሉ መንግሥት የድርሻውን እንዲወጣም ከወዲሁ ጠይቀዋል።
“ፋሲል ከነማን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ቡድኑን በገንዘብ ደግፎ ጠንካራ ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያን ስፖርት ቀድሞ ወደነበረበት የከፍታ ማማ ማድረስ እንደሚቻል አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here