“ጽኑ ሃይማኖት፣ ውብ ማንነት፣ ድንቅ ሥርዓት በወልቃይት”

0
69

ሁመራ: መስከረም 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ፀናች ሃይማኖታቸው አንገታቸውን ይሰጣሉ፣ ቃል ከሚፈርስ ሞታቸውን ይመርጣሉ፣ በቃል ኪዳን ይፀናሉ። በፀናች ሃይማኖታቸው ከፈጣሪያቸው ጋር ይገናኛሉ፣ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ይማፀናሉ፣ ብርታት፣ አንድነት ሰላምና ፍቅር በእየ እምነታቸው ለምድር ይሰጥ ዘንድ ይለምናሉ።

በሕግና ሥርዓት ያምናሉ፣ ሥርዓት ይሠራሉ፣ በተዋበው ሥርዓታቸው ይገዛሉ። ሰላቶና ሥርዓት አፍራሽን በሥርዓት ይቀጣሉ። ውብ ስለኾነች ማንነታቸው፣ ከአባት ስለወረሷት እውነታቸው፣ በቃል ኪዳን ስለ ተቀበሏት ሃቃቸው፣ ድንቅ ስለኾነች ባሕላቸው፣ ስለ ተከበረች ታሪካቸው ሲሉ ከሞት ጋር ታግለዋል፣ ከገዳይ ጋር ኖረዋል፣ የጨለመ በሚመስለው ዘመን ብርሃናቸውን ለመመለስ ተንከራትተዋል።

ብዙዎች በገዳዮች ወላጆቻቸውን አጥተዋል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ተነጥቀዋል፣ የቀዬው አድባርና ዋርካ የሚባሉት ወድቀው፣ በክፉዎች ሰይፍ አልፈው ቀዬው መካሪና ዘካሪ እንዲያጣ ተደርገዋል።

ተወልደው ባደጉበት ቀዬ፣ ፊደል በቆጠሩበት አፀድ ሥር፣ አንደበታቸውን በፈቱበት ልሳን ፈጣሪያቸውን እንዳያመሰግኑ ተከልክለው ኖረዋል። አቤቱ መልካሟን ቀን መልሳት፣ የክፉዎችን ልብ አራራት፣ ለክፋት የተዘረጉ እጆችን እጥፋቸው፣ በክፋት የተዘጉ ልቦችን በመልካምነት ቁልፍ ክፈታቸው፣ ስምህን ያለ ሰቀቀን የምንጠራበት፣ ክብርህን ያለ ስጋት የምንመሰክርበት ዘመን አምጣልን እያሉ ተማፅነዋል።

ከአፀዱ ሥር እየተቀመጡ ሲያነቡ ኖረዋል፣ ያለ በደላቸው በደልን ተቀብለዋል፣ ያለ ሐጥያታቸው ቅጣትን ተሸክመዋል። በበዓላት ጊዜ ሕዝብ የሚሰግድላቸውን፣
እየተባረከ በረከት የሚያገኝባቸውን፣ ከምንም በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸውን ታቦታት ይዘው እንዳይወጡ ተስፈራርተዋል፣ ቢያወጡ እንኳን ሃይማኖቱ የሚያዝዘውን ፣ መጽሐፉ የሚፈቅደውን፣ አምላክ የሚለውን እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም። በአደባባዩ እንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው ገዢዎችን የሚያስደስት ነበር እንጂ።

ተወልደው ባደጉበት ቀዬ እንደ ባዕዳ ተቆጠሩ፣ ሊለውጡት በማይችሉት ማንነት የግፍ ግፍ ተቀበሉ። ዘር የማይቆጠርባት፣ ብሔር የማይጠቀስባት፣ ሃብትና ፀጋ የማይጠየቅባት ሃይማኖት በባለጊዜዎቹ እጅ ተይዛ እውነተኛ አገልጋዮቿን፣ እውነተኛ እረኞቿን፣ እውነተኛ ታዛዦቿን አጥታ ኖረች።

ምዕመናኑ አስቀድመው ከሚያውቁት፣ ከአደጉበት፣ ከጥንት ጀምሮ ከቆዩበት ውጡ ሲባሉ ምን ሲደረግ አሉ። በቀደመው ባሕል እንደምቃለን፣ በቆየው ትውፊት እንዘልቃለን፣ በአባቶቻችን ወግና ሥርዓት እንገዛለን፣ በመዋቢያችን እንዋባለን አሉ። ባለ ጊዜዎች ግን ከለከሏቸው፣ ባለ ጊዜዎች ግን አሳደዷቸው፣ አዋከቧቸው፣ እኛ የምንሰጣችሁን ተቀበሉ አሏቸው። የማይመስልህን አትቀበል፣ የሚመስልህንም አትጣል ተብለው አድገዋል፣ እሺ ብለው ቃል ኪዳን ተቀብለዋልና አሻፈረኝ አሉ። ትቀበላለህ አልቀበልም በሚል የተነሳው ጠብ ለዓመታት ዘልቆ ንፁሐን በግፍ አለቁ።

ብዙዎች መዳረሻቸው ሳይታወቅ፣ እርም ሳይወጣላቸው፣ ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ ሳያለቅስላቸው እንደጠፉ ቀርተዋል፣ ብዙዎች በእስር ቤት ውስጥ እንዳሉ አሸልበዋል፣ ብዙዎች ተሰቃይተው ላይመለሱ አልፈዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰባቸው፣ ይህ ሁሉ ስቃይ እየወደቀባቸው ስለ እውነት ታገሉ እንጂ አንድም ቀን በርከክ አላሉም። ከኢትዮጵያዊነት ልክ ዝቅ አይሉም፣ በማይመስላቸው ሥፍራ አይውሉም።

እነዚህ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ደግና ኩሩ ጀግኖች ካለማንነት ማንነት ሲሰጣቸው አሻፈረን አሉ። የሕወሓት የሽብር ቡድን ከመመሥረቻው ዘመን ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ ሠማይ ሥር አያሌ በደሎችን አድርሷል። የሽብር ቡድኑን ዓላማና ዒላማ አስቀድመው ያወቁት ጀግኖች ታዲያ አስቀድመው ታገሉት፣ አምርረው ጠሉት፣ በጀግንነታቸው እና በፅናታቸው ጣሉት፣ ከዙፋን ወደ ዋሻ ወረወሩት።

ጠላታቸውን ከወረወሩት፣ በትግላቸው ወንዙን ካሻገሩት በኋላ በወልቃይት ሰማይ ሥር የቀደመው ውበት፣ የኖረው ማንነት፣ አባቶች የጠበቁት ሥርዓት፣ የሚያምኑት ሃይማኖት ያለ ከልካይ መድመቅ ከጀመረ ቆይቷል። በጌጣቸው ያጌጣሉ፣ በባሕላቸው ይዋባሉ።

እነሆ በዓለ መስቀል ደርሷል፣ በበዓለ መስቀል የመስቀሉ ፍቅር ይታወሳል፣ በመስቀሉ ላይ የተሰጠው ዋጋ ይወሳል፣ በመስቀል ድኅነትን፣ በመስቀል ኃይልን፣ በመስቀል ፀጋን፣ በመስቀል አሸናፊነትን፣ በመስቀል ከሙት መነሳትን፣ ከእሳት መውጣትን፣ ጠላት ድል መንሳትን የሰጠው ጌታ ስሙ ከዳር ዳር ይወሳል፣ ይወደሳል። በመስቀሉ ያመኑት፣ በመስቀሉ የዳኑት፣ በመስቀሉ ክፉውን በመልካም ነገር የለወጡት፣ በመስቀሉ ድልን የተቀዳጁት ሁሉ ስለ መስቀሉ ክብር ይመሰክራሉ፣ ከአንገታቸው ቀለስ፣ ከወገባቸው ጎንበስ እያሉ መስቀሉን ይሳለማሉ። ለመስቀሉ ይሰግዳሉ።

ክርስቲያኖች መስቀልን ምልክታቸው፣ መታወቂያቸው፣ ጌጣቸው ያደርጉታል። የድል መንሻቸው ነውና ከፍ ከፍ ያደርጉታል። በወረኃ መስከረም በ17ኛዋ ቀን ደግሞ መስቀልን በልዩ ድምቀት ያከብሩታል። ይህች ቀን ልዩ ቀን ናት። ድንቅ ነገር የተደረገባት፣ መልካም ነገር የሚታሰብባት፣ ተስፋና ብርሃን ያለባት።

በዓለ መስቀል በሚከበርባት በልዩ ቀን ወልቃይት ጠገዴ ዳንሻ ከተማ ተገኝቻለሁ። ደማቋ ከተማ በጠዋት ደምቃለች። ጎዳናዎቿ ነጫጭ በለበሱ ምዕመናን ተመልተዋል፣ ሕፃናት ተውበዋል፣ ካህናት በልበሰ ተክህኖ ተንቆጥቁጠዋል፣ ዲያቆናት ነጫጭ እርግቦች መስለዋል፣ የሰንበት ተማሪዎች ሃይማኖቱን በጠበቀ ድንቅ ውበት ተሞሽረዋል። ደማራው ተደምሮ በኩራት ቆሟል፣ ሊቃውንቱ ያመሰግናሉ፣ እናቶች እልልታውን ያደምቃሉ፣ የሰንበት ተማሪዎች ልብን በሚያንሰፈስፍ ዝማሬ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርባሉ። በደመራው አጠገብ ድንቅ ነገር ተደረገ። በዓይኖቼ እያማተርኩ፣ ድንቅ ሃይማኖት፣ ድንቅ ሥርዓት፣ ድንቅ ባሕል የተወደደ ደስታ ተመለከትኩ። በተመለከትኩት ሁሉ ተደነቅሁ። ተገርምኩም።

ሁሉም ተውቧል። አምሯል። የተነጠቁትን ያገኙት ደስታቸው ወደር አጥቷል። ዛሬ ላይ አጀባቸውን የሚያስተጓጉል፣ መንገዳቸውን የሚያስናክል የለም። ሁሉም በኩራት እና በኅብረት፣ በድንቅ ሥርዓት ይጓዛሉ፣ ይደምቃሉ፣ ያደምቃሉ እንጂ። የተገደሉባት፣ መከራ ያዩባት ሠንደቅ በደማራው ላይ አሸብርቃለች፣ በመቋሚያቸው፣ በየአደባባዩ ደምቃለች፣ በኩራት ትውለበለባለች። ፅኑ ሃይማኖት፣ ውብ ማንነት፣ ድንቅ ሥርዓት ወልቃይት ላይ ተመለከትኩ።

በድል መንሻው በዓል ድል ነስተው በደስታ አከበሩት። ምስጋና ለፈጣሪ አቀረቡለት፣ ስሙን ደጋግመው ጠሩት። ከፍ ከፍም አደረጉት።

በመስቀል በዓሉ የእስልምና አባቶችም ተገኙ። ያለ ሃይማኖት ልዩነት ማክበር ኢትዮጵያዊ ባሕሪ ነው፣ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው፣ ኢትዮጵያዊ ፀጋ ነው፣ ኢትዮጵያዊ ልክ ነው፣ ኢትዮጵያዊ መገለጫ ነውና። ዳንሻ እልል አለች፣ በደስታ ተጨነቀች፣ አጌጠች፣ በውበት ደመቀች። ፀሎቱና ምስጋናው ቀርቦ ደመራው ተባርኮ በአበው ሲለኮስ እልልታው ከቀደመው ሁሉ በለጠ። የደስታ ድምፅ ከዳር ዳር አስተጋባ። ለካስ ሁሉም በፈለጉት ሲኾን ነው ውበቱ ጎልቶ የሚወጣው፣ ለካስ ሁሉም በራስ መልክ ሲኾን ነው ግሩም ድንቅ የሚያስብለው። አሁን ሁሉም በራስ መልክና ባሕል ነውና ሁሉም ደምቋል።

በበዓሉ መልእክት ያስተላለፉት የደብረ ቅዱሳን አብረነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን አስተዳደሪና የወልቃት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ መምህር ሰሎሞን አቡሃይ ሁላችን በጋራ ሥንሠራ ሀገራችን መጠበቅ፣ ሉዓላዊነቷን ማስከበር እንችላለን ብለዋል። በዓላት የሚከበሩት ነፃነት ሲኖር ነው፣ በየጊዜው መጥፋት አለባቸው፣ ነፃነታቸውን ማጣት አለባቸው የምንባል ሕዝቦች ነን ያሉት መምህሩ በአንድነት እና በፅናት ከቆምን ጠላቶቻችን አቅም ያንሳቸዋል ብለዋል። ሕዝቡ ሁሉ ቃል ኪዳኑን እንዲጠብቅ፣ ሃይማኖቱን እንዳይጥል፣ ክብሩን እንዳይረሳ አሳስበዋል። ክብሩን የረሳ፣ እሴቱን የተወ፣ ፈርዓ እግዚአብሔር የሌለው ይወድቃል፣ ይናቃል ነው ያሉት።

መስቀል የፍቅር በዓል፣ መስቀል የአንድነት፣ መስቀል የማሸነፍ በዓል እንደኾነ ያነሱት መምህሩ ሁሉም በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያን ችግር ሊያበዙባት የሚጥሩትን ጠላቶች በጋራ መታገል እና ሀገርን መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።

የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ስልጣን አድማሴ በዓልን በነፃነት ማክበር ልዩ ትርጉም እና ስሜት እንዳለው ነው የተናገሩት። የሽብር ቡድኑ በነበረበት ዘመን በዓላቱን ለማክበር አስቸጋሪ እንደነበርም አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ከጠላት ነፃ የኾነች ሀገር እንድትኾን ሀገርን እየተከላከለ ለሚገኘው ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ብርሃን የሁሉም ነው ያሉት ከንቲባው ብርሃነ መስቀሉን በጋራ አክብረነዋልም ብለዋል።

እልልታውና ደስታው እንደ ደመቀ ይውላል። ለምን በዓለ መስቀል ነውና። እንኳን አደረሳችሁ።

በታርቆ ክንዴ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J