ጮቄ በውበትና ክብሩ ልክ እየለማ እንዳልኾነ የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

112

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ በምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች መካከል ስድስት ወረዳዎችን እና 22 ቀበሌዎችን አካልሎ አርፏል። የጥብቅ ስፍራው አብዛኛው አካል ግን በምሥራቅ ጎጃሙ ስናን ወረዳ ላይ ያረፈ ነው። ጮቄ ተራራ 4 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ የውኃ ቋት ነው።

የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው የጮቄ አጠቃላይ ስፋቱ 53 ሺህ 558 ሄክታር ነው። በጥብቅ ደንነት የተከበረው ግን 6 ሺህ 24 ሄክታር የሚኾነው ብቻ ነው።

ጮቄ “የጎጃም ጣሪያ” እየተባሉ በሚሞገሱ ተራራዎች ልዩ ውበትና ተፈጥሮአዊ ጸጋ የተላበሰ፣ በዕፅዋት እና እንስሳት ብዝኃነትም የታደለ ነው። ከ85 በላይ ሀገር በቀል ዕፅዋት ቤታቸው በጮቄ ነው። የጮቄ ተፋሰስ የታችኛው ክፍል ሾላ፣ ሎል፣ ክትክታ፣ ግራር፣ ቅላባና አምቡስ በመሳሰሉ ዕፅዋቶች የተሸፈነ ነው፡፡ የላይኛው ተፋሰስ ደግሞ ጅብራ፣ጓሳ፣ አስታ፣ ቀርቀሃ፣ አምጃ፣ አሸንግድየ፣ ዝግባ/ግምይ/  እና በመሳሰሉ ሀገር በቀል ዕፅዋት እና ዛፎች የታጀበ ነው።

የጮቄ ሌላው ልዩነቱ የአፍሪካ የውኃ ማማነቱ ነው። 273 ትናንሽ ጅረቶች እና 23 ትላልቅ ወንዞች መነሻቸው ከጮቄ ነው። እነዚህ ወንዞች በአፍሪካ ብሎም በዓለም ስሙ ለገነነው የዓባይ ወንዝ ኹነኛ ገባሮች ናቸው። የዓባይ ውኃ ወደ 10 በመቶው በእነዚህ ጅረት እና ወንዞች አማካኝነት ከጮቄ ተቀድቶ የሚሞላ ስለመኾኑም መረጃዎች ያመላክታሉ።

የጮቄን ውበት ዓለም ራሱ መስክሮለታል። በዚሁ ድንቅ ስፍራ ጉያ የሚገኘው የጮቄ ቱሪዝም መንደር በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የ2022 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብሎ ዕውቅና ተሰጥቶት በክብር እንደተሸለመም ይታወሳል። የጮቄ ስምና ክብር በዓለም ላይ የዋለ ነው።

ታዲያ ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም ዓይን ማረፊያ የኾነው ይህ ድንቅ ስፍራ እንዴት እየተጠበቀ ይኾን? አሚኮ በቦታው ተገኝቶ እየተደረገ ያለውን እና ሊኾን የታሰበውን የጮቄ ጥበቃ እና እንክብካቤ ተመልክቷል።

ሥለ ጥብቅ ስፍራው አያያዝ ሃሳባቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የጮቄ ነዋሪ  “ያለ ጮቄ እና ያለ ከብቶቻችን አንኖርምና ተውን” የሚል አጭር መልስ ነው የሰጡን። አማራጭ የኢኮኖሚ መሰረት እስካልተበጀ ድረስ ጮቄን ከነዋሪዎች የእንስሳት ግጦሽነት መከልከል የብዙ ቤተሰቦችን ኑሮ ሊያናጋ ይችላል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርነው ነዋሪ አጭር ምላሽ ሲተነተን ይህንኑ ያስረዳል። ያገኘናቸው ሌሎች ነዋሪዎች ግን ለማነጋገር እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም።

የጮቄ ማኅበረሰብ የጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላልኝ ጎሹ እንደነገሩን እና እኛም በአካል ተገኝተን እንደታዘብነው አሁናዊው  እንክብካቤ እና ጥበቃ የጮቄን ክብር እና ገናናነት የሚመጥን አይደለም። ጥብቅ ስፍራው ከቤት እንስሳት ልቅ ግጦሽ ነፃ መኾን እና የዕጽዋት እና እንስሳት ብዝኃነቱ  የተረጋገጠ መኾን አለበት። ጮቄ ግን “በእጅ የያዙት ወርቅ…” እንዲሉ አበው፤ በተፈጥሮ ያገኘውን እድል በሰዎች ያልተገባ ድርጊት የተነጠቀ ኾኗል።

ጮቄ በአካባቢው አርሶ አደሮች የቤት እንስሳት እየተወረረ ገላው ከልቅ ግጦሽ አልዳነም። በአርሶ አደሮች አይፈረድ ነገር ዘመናትን የተሻገሩበት የኑሮ መሰረታቸው ይሄው የእንስሳት እርባታ ነው። ኑሮአቸውም የተመሠረተው ከእንስሳት ጋር በተያያዘ ነው።

እንደ አቶ ሞላልኝ ገለጻ የአካባቢው አርሶ አደሮች የቤት እንስሳትን በጮቄ ላይ እንዳያሰማሩ ቢከለከሉም፤አርሶ አደሮቹ የኖሩበትና እያኖራቸው ያለውን የእስሳት እርባታ ዘዴ ይሄው ነውና ክልከላውን በጀ አላሉም። የአርሶ አደሮችን ኑሮ ከጥብቅ ስፍራው ጋር አጣጥሞ ለማስቀጠል ጮቄን የማይበድል ሌላ ዓይነት ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ አለያም ደግሞ በምትኩ አማራጭ የሥራ መስክ ሊፈጠርላቸው ይገባል። ይህ ባለመኾኑ ግን የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራን ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ለማድረግ እና የብዝኃ ሕይወቱን መመናመን ለማስቀረት አዳጋች አድርጎታል ብለዋል አቶ ሞላልኝ።

እንደ ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ገለጻ የኑሮ መሠረታቸው የግድ ጮቄ ላይ ከኾነ ነዋሪዎች ሌላ፤ ጥብቅ ደኑን በአልጠግብ ባይነት ለመውረር የሚሞክሩም አሉ። ጮቄን ከእነዚህ አካላት ለመጠበቅ የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ ሞላልኝ ተናግረዋል። ለአብነትም በወረራ ተይዞ የነበረ 547 ሄክታር የጥብቅ ስፍራውን መሬት ማስለቀቅ ተችሏል ብለዋል። ጮቄን ተጋፍተው የተገነቡ 110 ቆርቆሮ ቤቶች እና ከ426 በላይ ሳር ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉንም አቶ ሞላልኝ ተናግረዋል።

አቶ ሞላልኝ በአካባቢው የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጮቄን የመጠበቅ ማኅበራዊ ኀላፊነት ወስዶ ሥራዎችን አየሠራ ቢሆንም  ቃል የሚገባውን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከተ አይደለም ብለዋል።

ይህንን ጉዳይ ይዘን ወደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አቀናን። የዩኒቨርሲቲው የጮቄ ተፋሰስ ምርምርና ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምግባር ወንዴ (ዶ.ር) ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሚችለው መጠን ጮቄን የመጠበቅ ማኅበራዊ ኀላፊነት እየተወጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል። “የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ተግባር የመማር ማስተማር ሥራ ማከናዎን ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት እና ምርምር ሥራዎችንም በዋናነት እያከናወንን ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የጮቄን ችግሮች በምርምር በመፍታት እና ለማኅበረሰቡ ዕውቀት በማካፈል እያገዘ መኾኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ምግባር  አርሶ አደሮች ከተለመደው አሠራር ወጥተው ከጮቄ ጋር ወደሚዛመድ የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከስድስቱ አዋሳኝ ወረዳዎች ውስጥ እንደ ማሳያ በሦስቱ ማለትም በሰዴ ፣ ደባይ ጥላት ግን እና ቢቡኝ ወረዳዎች 1 ሺህ ወጣቶች ከቁም እንስሳት እርባታ ወጥተው በንብ ማነብ ላይ ተሰማርተዋል ብለዋል። በዚህም የበለጠ ጥቅም እያገኙበት መኾኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ለነዋሪዎች ግንዛቤ በመፍጠር ጮቄን በማይጎዳ እና ከልቅ ግጦሽ በሚያላቅቅ የሥራ መስክ ለማሰማራት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 30 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሠራ ስለመኾኑም ዶክተር ምግባር ገልጸዋል። ይህንን አይነት አማራጭ የኢኮኖሚ ምንጭ በሁሉም የጮቄ አዋሳኝ ወረዳዎች በማስፋት አርሶ አደሩ በጮቄ ላይ የሚያደርሰውን ልቅ ግጦሽ በዘላቂነት የመከላከል ሥራ በትኩረት እንደሚከናዎንም ተናግረዋል።

ጥብቅ ስፍራው የአፍሪካ የውኃ ማማነቱ ተጠብቆ ውበት እና የተፈጥሮ ጸጋው የዓለምን ዓይን የበለጠ እያማለለ ለተሻለ ኢኮኖሚ ምንጭ ይኾን ዘንድ ማኀበረሰቡ ጮቄን ከሚጎዱ ድርጊቶች መታቀብ እንዳለበትም ዶክተር ምግባር አሳስበዋል። ልቅ ግጦሽ፣ የደን መጨፍጨፍ፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት መመናመን፣ እንዲሁም በአካባቢው ባሉ አርሶ አደሮች እርሻና በመኖሪያ ቤት መወረርን መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ውድዓለም አልማው ጮቄ የዞኑ ሁነኛ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ነው ብለዋል። የዞኑ ቱሪዝም መምሪያ መዳረሻውን የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እያከናወነ የቆየ ስለመኾኑም ወይዘሮ ውድዓለም ተናግረዋል። ይሁን እንጅ በአካባቢው የሆቴል አገልግሎት አለመኖሩ ቦታው በጸጋው ልክ እንዳይጎበኝ አድርጎታል ነው ያሉት።

የተፈጥሯዊ ውበት እና ማራኪ ገጽታ ባለቤት ወደኾነው ጮቄ ጎብኝዎችን በመሳብ የጸጋው ተጠቃሚ ለመኾን እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ባለሃብቶች ለቱሪስት የሚመጥኑ ሆቴል እና ሎጅዎችን በአካባቢው በመገንባት ራሳቸውን፣ አካባቢውን እና ሀገርን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ወይዘሮ ውድዓለም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!