“ጫካ ውስጥ የሚኖረው አምበሳ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም፤ ለዚህም አድዋ ምስክር ነው!”

91

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለራሳቸው የሚሰጡት የተሳሳተ ግምት እና ትርክት ገደብ የለውም፡፡ ምዕራባዊ ሆኖ መፈጠር ምሉዕነት ተደርጎ የተሳለበት ወቅት ሩቅ ነው፡፡ ለረጂም ዘመናት ሌላው ዓለም በእነርሱ ዘንድ ዋጋ ቢስ ተደርጎ ሲቆጠርም ቆይቷል፡፡ ንቀታቸው ንቃት የሚመስላቸው አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ጽንፈኛ የፖለቲካ ልሂቃን የቀሪው ዓለም ትህትና እና ግብረ ግብነት አላዋቂነት እና ፍርሃት ይመስላቸዋል፡፡

ገና በዓለም ሕዝቦች ማለዳ በፍጡራን መካከል የቆዳ ቀለም እና እምነትን መሰረት አድርገው ለሰው ልጆች ደረጃ አወጡ፡፡ እርሱን ተከትሎም አሳዳጅ እና ተሳዳጅ ተፈጥሮ፤ አሳዳሪ እና ሎሌ ተለይቶ ሰላማዊው ሕዝብ “የዓለም ጦርነት” የሚል ስያሜ በተሰጣቸው ግጭቶች ውስጥ እንዲያልፍ ተደረገ፡፡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጎራ በለየ የዓለም ጦርነት ውድ ሕይዎት ተገብሯል፤ ሃብት ንብረት ወድሟል፤ ጥፋቱን ተከትሎም በርካታ ሀገራት ለዘመናት በድህነት እንዲማቅቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት ተፈጥሮ የሕዝብ ሰቆቃ እና እልቂት እንዲፈጠር አንዱን የበላይ ሌላውን ተከታይ የሚያደርጉ ኅይሎች ምክንያት ሆኑ፡፡ ለዘመናት በሁለት ጎራ የተከፈለችው ዓለም የምሥራቁ እና የምዕራቡ ኃይሎች ተብሎም የልዩነት ደንበር እና የጥላቻ አጥር ተዘጋጀላት፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ “እኛ የተለየን ዘሮች ነን” ባሉ ልሂቃን እና ሃሳቡን በተቀበሉ ተከታዮቻቸው ምክንያት ነበር፡፡

የሚገርመው ግን ልክ የሌለው ንግግራቸው እና የተንሸዋረረው እይታቸው አሁንም ድረስ አብሯቸው እንደዘለቀ መሆኑ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንግሊዝ ውስጥ አንድ የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ማስመረቂያ ሥነ ስርዓት ላይ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ ኅላፊ ጆሴፍ ቦሬል ባደረጉት ንግግር “አውሮፓ በጥንቃቄ የተዘጋጀ የአትክልት ስፍራ ነው፤ ሌላው ዓለም ግን አሁንም ድረስ ጫካ ነው” ሲሉ መደመጣቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሰውየው ንቀት የተሞላበትን እና ሥርዓት የጎደለውን ንግግራቸውን ቀጥለውም “አውሮፓ በጥንቃቄ የተዘጋጀ የአትክልት ስፍራ ነው፡፡ ሌላው ዓለም ግን አሁንም ድረስ ጫካ ነው፡፡ ጫካው የአትክልት ስፍራውን ሊወርር ተዘጋጅቷል፡፡ የአትክልት ስፍራው ባለቤቶች በጥንቃቄ ያዘጋጁትን ስፍራ ከጫካው ከወጡ ወራሪዎች የመጠበቅ ኅላፊነት አለበት” ሲሉም ግልጽ ጦርነት አወጁ፡፡ ለቅው ዓለም ያላቸውን የለየለት ንቀትም በይፋ አወጡት፡፡

ጆሴፍ ቦሬል ንግግራቸውን ሲያደማድሙም የጫካው ባለቤቶች አደገኞች እና አቅማቸውን እያሳደጉ ነው ካሉ በኋላ በመጨረሻም “እነርሱ ወደ አትክልት ስፍራው ከመምጣታቸው በፊት እኛ ወደ ጫካው መሄድ ይኖርብናል” ሲሉ ተደመጡ፡፡ ይህ ከትንኮሳ እና ንቀት ያለፈ ግልጽ ወረራ እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ነው የሚሉትም በዝተዋል፡፡

እውቁ ሩሲያዊ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ የሰውየውን ንግግር አስመልክቶ ሲናገሩም “አዲስ ነገር የለም፡፡ ምዕራባዊያን ለዘመናት በህቡዕ ሲሰሩት የነበረውን እና የሚያራምዱትን የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ቦሬል በፍርሃት አለበለዚያም በስሜት በግልጽ አወጡት” ይላሉ፡፡ የሰውየው ንግግር ምዕራባዊያን በዲፕሎማሲ ስም በቀሪው ዓለም ላይ በቀጣይ ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ ፍንጭ የሰጠ ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ አካሄዳቸው የዘመናዊው ቅኝ ግዛት አዲስ ቅኝት እንደሆነ ይሰማኛል ይላሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ እብሪት በወጠራቸው እና ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር ባለባቸው ኅይሎች መካከል የሚደረገው ፍልሚያ የማይቀር ይመስላል ካሉ በኋላ ራስን ማዘጋጀት እና መስመርን መለየት የጫከው ኅይሎች ፋንታ ነው ይላሉ፡፡ ትናንት በአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፊት ለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይም የሰውየውን ስም ጠቅሰው “ጫካ ውስጥ የሚኖረው አምበሳ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም፤ ለዚህም አድዋ ምስክር ነው!” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!