ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመከላከል፣ ወረርሽኙ ለሚያስከትላቸው ዘርፈ ብዙ ተጽእኖዎችና ሌሎችም ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠጥ መንግሥት ማብራሪያ እንዲሰጥ የምክር ቤት አባላቱ ጠየቁ፡፡

139

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እያካሄደ ነው፡፡

ልዩ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) በተገኙበት ነው እየተካሄደ የሚገኘው፤ የምክር ቤት አባላትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄችን እያቀረቡ ነው፡፡

የምክር ቤት አባላት ጣና ሃይቅን የወረረውን እምቦጭ አረም ትኩረት ሰጥቶ ለመከላከል በመንግሥት በኩል ስለታሰቡ እቅዶች፣ የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የዋጋ ንረቱ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመከላከል ምን እየተሠራ እንደሆነ፣ ወረርሽኙ በግብርና ሥራውና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳያሳድር የተያዙ እቅዶች ምን እንደሆኑ ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አቅርበዋል፡፡ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሕዝቡን ለማደናገር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሥርዓት ለማስያዝ በመንግሥት በኩል ምን እንደታሰብም ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ ዜጎችን እየፈተነ በመሆኑ ወረርሽኙን ለመግታት ከሚሠራው ተግባር ባለፈ የእነዚህ ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለማድረግ ምን እየተሠራ እንደሆነም የምክር ቤት አባላቱ ጠይቀዋል፡፡

ከሱዳን፣ ከጅቡቲና ሶማሊያ ጠረፍ አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎችን ለመቆጣጠርና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከክልሎች ባለፈ የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ የሚሻ በመሆኑ በዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡