“ጎንደር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታላቅ እና ገናና ታሪክ የከተመባት ጥንታዊ መናገሻ ናት፤ የአባቶቻችሁን ባሕል እና ወግ ጠብቃችሁ እንግዶቻችን የተቀበላችሁበት መንገድ አስተማሪ ብቻ ሳይኾን አኩሪ ገድልም ነው” ዶክተር ይልቃል ከፋለ

70
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር: ጥር 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ቀን ክርስቲያኖች በየዓመቱ በድምቀት ያከብሩታል፡፡ በዓሉ በመላው ዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ቢኾንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በተለየ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡

የ2015 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ጎንድር ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) “የጥምቀት በዓል መልዕክቴን ሃይማኖት እና ታሪክ ከከተመበት ጥንታዊው የፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ላይ ሆኘ ሳስተላልፍ ደስታየ ወደር የለውም” ብለዋል፡፡

ጥምቀትን በጎንደር መታደም ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል እና ማንነት በአንድ የሚታዩበት አውድ በመኾኑ መታደል ነው ብለዋል፡፡

ጎንደር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታላቅ እና ገናና ታሪክ የከተመባት ጥንታዊ መናገሻ ናት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የአባቶቻችሁን ባሕል እና ወግ ጠብቃችሁ እንግዶቻችን የተቀበላችሁበት መንገድ አስተማሪ ብቻ ሳይኾን አኩሪ ገድልም ነው ብለዋል፡፡

ጎንደርን ስናስብ ቱሪስት ቀድሞ ወደ አዕምሯችን ይመጣል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በሚገባ ሠርቶ እና ጎብኝዎችን አቆይቶ የተጎዳውን የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ማነቃነቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ቆማችሁ የምትሰሩ የክልሉ ወጣቶች ስላደረጋችሁት ጉልህ አበርክቶ የክልሉ መንግሥት የላቀ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን እና መሰል አኩሪ እና አስተማሪ ትውፊት ለዘመናት ጠብቃ ከዚህ ስላደረሰችልን እያመሰገንን መንግሥት በዓላቱ ካላቸው ሃይማኖታዊ የትውልድ ግንባታ ፋይዳ በተጨማሪ የሀገሪቱ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆኑ እንሠራለን ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!