“ጎርጎራ ማን አገኘሽ? ማን ደበቀሽ? ማንስ አየሽ?”

43
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ጎንደር: ታኅሣሥ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንቺ ውብ ምድር የውበትሽን ነገር ማን አየሽ? ማንስ ሰፈረብሽ? ማንስ ከተመብሽ? ማንስ ገደመብሽ? ማንስ አስዋበሽ? ማነው ታላቅነትሽን የመሰከረልሽ? ጠቢባኑ ከጥበብ ባለቤት ጥበብን ተቀብለው ምድርን በጥበብ ይመረምራሉ፣ ሰማይን በጥበብ ያስሳሉ፣ መልካሙን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ።
ጠቢባኑ አዩዋት፣ አይተውም ወደዷት፣ በተወደደችውም ምድር የተወደደችውን አነፁባት፣ ከመወደድ ላይ ሌላ መወደድ ጨመሩባት። እርሷም ተወድዳ ተመሠረተች፣ ስትወደድ ኖረች፣ እየተወደደች ትኖራለች። በሐይቅ ዳር የሠፈረች፣ እርጋታና ሰላምን የተቸረች፣ በውበት የተጎናፀፈች ውብ መንደር። የደከማቸው ብርታትን ያገኙ ዘንድ ሄዱባት፣ በሐይቁ ዳር ተቀምጠው ደስታን እና ብርታትን ገበዩባት። ከተጨነቀ መንፈስ ራቁባት፣ ተስፋ ካጣ ዘመን አመለጡባት፣ ታላቁን ተስፋም ወሰዱባት።
በዙሪያ ገባዋ የሚኖሩ አበው ጸሎት ይጠብቃታል፣ ሰላምን ይሰጣታል፣ ከመወደድ ላይ ሌላ መወደድ ይደርብላታል። በሰርክ ከገዳማቱ የሚወጣው መልካም ማዕዛ ያጥናታል፣ ቡራኬው ይባርካታል፣ በረከቱ ያንዣብባታል፣ ተወዳጅም ያደርጋታል። በዚያች መንደር ፍቅርና አንድነት ሞልቷል። የበዛ በረከት ታድሏታል።
በረሃ የከረሙት ወታደሮች ለእረፍት ጊዜያት ይመርጧታል፣ በበረሃ የዛለ ጉልበታቸውን፣ በምሽግ የከረመ አካላቸውን ያሳርፉ ዘንድ ይገሰግሱባታል፣ በደረሱም ጊዜ በአማረው ሐይቅ ዳር ተቀምጠው፣ በዙሪያ ገብ ባሉ ገዳማት የሚሰማውን የአበውን ጥዑመ ዜማ እያዳመጡ፣ ምድራዊ ያልኾነውን መልካም ሽቶ እያሸተቱ እርጋታ በተመላባት ምድር መልካሙን ጊዜ ያሳልፋሉ፣ በዚያች መንደር መንፈሳዊነት ያይላል። ነጋዴዎች ማርና ቅቤውን፣ ጤፍና ዳጉሳውን እየጫኑ ያራግፉባታል፣ በታንኳና በጀልባ ይመላለሱባታል። ጀልባዎችም ለማረፊያነት ይመርጧታል። ተጓዦችም መልካሙን ጊዜም ያሳልፉባታል። ሹማምንቱ ከቤተመንግሥታቸው እየወጡ ያርፉባት፣ መልካሙን ጊዜም ያሳልፉባት ነበር።
በዚያ በቀደመው ዘመን መነሻውን ከአስመራ ያደረገው ሜሎቲ ቢራ ይጫንባት፣ ከወደቧም ይራገፍባት ነበር። ወደቧ ጊዜ አልነበረውም፣ በተገዢውና በሸኝው ትርምስ፣ በእቃው ጋጋታ፣ በጀልባዎቹ መሄድ መምጣት ሥራ እንደበዛባት ውላ ሥራ እንደበዛባት ታድር ነበር። በቀይ ባሕር አቋርጦ፣ አስመራን ረግጦ፣ በስሜን በጌምድር የሚመጣው ውድ እቃ ይጫንባት፣ በወደቧ ይሸጋገርበት ነበር ታሪካዊቷ መንደር ጎርጎራ።
ጎርጎራ ኾይ አስቀድሞ ማን አየሽ? ማንስ አስዋበሽ? በመካከል ማንስ ደበቀሽ? ማንስ በድጋሜ አየሽ? ከተደበቅሽበት አወጣሽ? ጎርጎራ ከታላቋ ገዳም ጋር የተሳሰረ ታሪክ እንዳላት ይነገርላታል። ውበቷ፣ ታሪኳ ከእርሷ ጥላ ሥር ነውና። ያቺ በእሳር ጎጆ ዘመናትን የተሻገረች ገዳም ለጎርጎራ ብዙ ነገሯ ናትና። ምዕራፈ ቅዱሳን ጽዮን ደብረ ሲና ማርያምን ጥላ አድርጋ ተመሰረተች፣ በእርሷው ጥላ ሥር ለዘመናት በአያሌ ታሪክ አለፈች፣ እልፎችን እየተቀበለች፣ እልፎችን እየሸኘች ኖረች፣ ዛሬም እልፎችን እየተቀበለች እልፎችን ትሸኛለች። ጎርጎራ የታሪክ እና የብርቅ ነገሮች መገኛም ናት።
የ93 ዓመቱ አዛውንት ጎይቶም ገብረአምላክ ጎርጎራ የጦር ሠራዊት መናኸሪያ ነበረች ይሏታል። የበዙ ገደማት ስላሏት ብዙ ሰዎች ይጎበኟታል። እርሷ የሱሲንዮስ ከተማ ናትም ይሏታል። ሱሲንዮስ ይወዷት ነበር። በእርሷ አጠገብም ያመረ ቤተ መንግሥት አንፀው ነበር። በኃይለ ሥላሴ ሙሉ ነበር የሚሉት ጎይቶም የጎርጎራ ወደብ ታላቅ በነበረበት እኔም እሠራ ነበር ነው ያሉን። “ስንቱ እቃ ተመላለሰባት፣ ስንቱን ሸኘነው፣ ስንቱንስ ተቀበልነው፣ የነጋዴው ብዛት፣ ከአስመራ የሚመጣውን የሚቀበለው፣ ወደ አስመራ የሚጭነው፣ በጣም ብዙ ነበር” ይላሉ አቶ ጎይቶም በትውስታ ወደ ኋላ እየከነፉ።
በኋላ ግን ነጋዴዎች እየቀሩባት፣ እየተዋት ሹማምንቱም እየረሷት እየደከመች መጣች። ጎርጎራ ቀደም ሲል በነበራት ግለት ቀጥላ ቢኾን ኖሮ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ከተማ ትኾን እንደነበርም አቶ ጎይቶም ነግረውናል።
የጎርጎራና አካባቢዋ አስጎብኚ እንደሻው ሰጠኝ ጎርጎራ ከታላቋ ገዳም ምዕራፈ ቅዱሳን ጽዮን ደብረ ሲና ማርያም በኋላ የተመሠረተች ናት ይላሉ። ጎብኚዎች የሚወዷት፣ የአካባቢውን ታሪክ ለማወቅና ለማጥናት የሚመርጧት ናት። ከመናገሻዋ ከተማ ጎንደር ተነስተው ወደ ጎርጎራ ይወርዳሉ፣ በዚያ ያለውን ድንቅ ነገር ያያሉ። በጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትንም ይጎበኛሉ። እርሷ ለየብስም ለባሕርም የተመቸች ናትና። እንደ አሰብ እንደ ምፅዋ ሁሉ የወደብ ከተማ ነበረች።
ዘመን ሄዶ ዘመን መጣ። የደርግ ሥርዓት ወደ ስልጣን መጣ። መሪው መንግሥቱ ኃይለማርያምም ያችን ውብ ሥፍራ ወደዷት። በፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅግ የተወደደችው ሥፍራም በዚያ ዘመን የሹማምንቱ መዳረሻ ኾነች። ፕሬዝዳንቱ የጎንደር ሕዝብ መዝናኛ ብለው መዝናኛ አሠርተው እንደነበርም አስጎብኝው እንዳሻው ነግሮናል። እርሳቸው ያሠሩት መዝናኛም አሁን ያለው ፕሮጀክት እስኪጀምር ድረስ መዝናኛ ኾኖ ያገለግል ነበር። ሹማምንቱ ጥሩ ጊዜ ያሳልፉባት ነበር። የጎርጎራ ወደብም ከፍተኛ መተላለፊያ ነበር። የደርግ ሥርዓት አልፎ ቀጣዪ ሥርዓት ሲመጣ ግን ጎርጎራ ተረሳች። አስታዋሽ አጥታ፣ ከመንግሥቱ እና እርሳቸውን ቀድመው ከመጡ ነገሥታት ጋር የነበራትን ትዝታ ታቅፋ ለዓመታት ኖረች። ነገሥታቱ በኋላም መንግሥቱ ያደረጉላትን እያስታወሰች፣ የምትታይበት ዘመን ዳግም እስኪመጣ ጠበቀች።
ጊዜ ሄዶ ጊዜ መጣ ጎርጎራን የረሷት ተረሱ። ጎርጎራን የሚያስታውስ ጊዜም መጣ። አሁን ላይ በጎርጎራ ሰማይ ሥር ውብ ፕሮጄክት እየተሠራ ነው። ያም ፕሮጄክት ጎርጎራን ከትካዜዋ እያወጣት፣ ከዝምታዋ እያሰነሳት መኾኑን አስጎብኚው ነግረውናል። ወደ ጎርጎራ በሄዱ ጊዜ ድንቅ ነገር ያያሉ፣ በከበቧት ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሥፍራዎች ይደመማሉ። ጎርጎራ የአንድነት መልክ ይሏታል። ለምን ከኢትዮጵያ ከአራቱም ንፍቅ የመጡ መታደሮች በፍቅር እና በአንድነት ይኖሩባታል እና። የጎርጎራ የመኖሪያ መርህ ፍቅር ነው። ፍቅር ካለ ሁሉም አለ። ፍቅር ስላላት ሁሉም ወደዳት። ሁሉም አያት።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም እና ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋሴ አስናቀው ትኩረት ተሰጥቷት ባለመቆየቷ በታሪኳ ልክ ማደግ ሳትችል መቆየቷን ተናግረዋል። የጎብኚዎችን ቀልብ የምትስብ ሃብት ያላት ኾና በድንቅ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ብትከበብም ለጎብኚዎች የተመቸ ማረፊያ ሳይኖራት ቆይታለች። ባለሃብቶችም በጎርጎራ እንዲሠማሩም ጠይቀዋል። ጎርጎራ ተረስታ የኖረች፣ አሁን አሁን ደግሞ እየታወሰች ያለች ከተማ ናት። አሁን አሁን የሚያዩዋት ባለሃብቶች እየተበራከቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ይዘው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለጎርጎራ መልካም ነገር ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል። ጎርጎራ በታሪኳ ልክ ከፍ እንድትል እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። መሄድስ ደምቢያ ከጣና ዳር፣ ከውቧ ምድር። ጎርጎራ የብዙ ሕልሞች መንደር፣ የፍቅር አድባር።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!