ጎሕ ቤቶች ባንክ በባሕር ዳር ከተማ አገልግሎት መሥጠት ጀመረ።

0
325

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የቤት ብድር አቅራቢ የኾነው ጎሕ ቤቶች ባንክ በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በመክፈት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

ባንኩ በሀገር አቀፍ ጀረጃ ከጥቅምት/2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲኾን በባሕር ዳር ደግሞ አምስተኛውን ቅርጫፉን ከፍቶ በዛሬው እለት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ሙሉጌታ አስማረ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የሚታየውን የቤት ችግር ለመቅረፍ ባንኩ እስከ 30 ዓመት የሚከፈል የቤት መግዣ ፣ የቤት መገንቢያ፣ የቤት ማደሻ እና የቤት ማሻሻያ የብድር አገልግሎት ቅድሚያ ለመስጠት የተቋቋመ ነው።

ደንበኞች ከባንኩ የብድር አገልግሎት ለማግኘት ከ30 በመቶ ጀምሮ ቁጠባ በመቆጠብ 70 በመቶ የሚኾነውን ባንኩ የሚያበድርበት አሠራር መመቻቸቱን ገልጸዋል። ከ14 እስከ 15 በመቶ የወለድ ምጣኔ እንደሚኖረውም ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል። ደንበኞች የመንግሥት ሠራተኛ ከኾኑ ከሚገነቡት ቤትና ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ከሚደረግላቸው የማስረጃ ድጋፍ ባለፈ የተለየ ዋስትና እንደማይጠየቁ ለአብነት አንስተዋል።

ባንኩ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ከሚሰጠው ብድር በተጨማሪ ሌሎች ባንኮች የሚሰጡትን የቁጠባና ሌሎች አማራጮችንም ይሰጣል። ደረጃቸውን በጠበቁ ቤቶች ግንባታ ዘርፍ በመሳተፍ የራሱን አስተዋፆኦ ማበርከት ከቀጣይ ዕቅዱ አንዱ ነው።

ጎሕ ቤቶች ባንክ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ካፒታል የተመሰረተ ሲኾን እስካሁን ግማሽ ቢሊዮን ብር ለተጠቃሚዎች የብድር አገልግሎት መሰጠቱን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) እንዳሉት በዚህ ዓመት 4 መቶ ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ለ824 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተሰጥቷ። ይሁን እንጂ የተላለፈው ቦታ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖረው ማሕበረሰብ በመኾኑ ባንኩ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት መገንባት ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ አቅም መኾኑን አንስተዋል። በከተማ አሥተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለበት የማኅበረሰብ ቁጥር ከፍተኛ በመኾኑ በቀጣይ የባንኩን የአክሲዮን ሽያጭ በማስፋት የማበደር አቅሙን በማጎልበትና ሌሎች አበዳሪ ተቋማትን በመሳብ ችግሩን መፍታት ይገባል ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም ለአበዳሪ ተቋማቱ ምቹ ኹኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ የሚሠራ ይኾናል። የአበዳሪ ተቋማት አቅም እየተጠናከረ ሲሔድ ከተማ አሥተዳደሩ ከክልሉ ጋር በመነጋገር መሬት ቆጣቢ የኾነ የቤት ልማት ስትራቴጅ በመንደፍ የነዋሪዎችን የቤት ችግር በጥናት እንደሚመልስ ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በቅርቡ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ባለቤት የኾኑት አቶ ማስረሻ በላይ፤ ጎሕ ባንክ በባሕር ዳር ከተማ ሥራ መጀመሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል። የመኖሪያ ቦታ ለደረሳቸው በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት በመገንባት የቤት ባለቤት ያደርጋል፤ የመኖሪያ ቤት እጥረትንም ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/