“ግዮን የወንዝ ቅዱስ፤ የሀገር ንጉስ”

0
70

ባሕርዳር፡ ጥር 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከአርባ ጊዜ በላይ ስሟ በመጽሃፍ ቅዱስ በመልካም ነገር ሁሉ ይነሳል የሚባልላትን ኢትዮጵያ ቀድሞ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ያስጠራት ከማህጸኗ የሚወጣው ቅዱስ ወንዝ ነው፡፡ ገነትን ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት መካከል ግዮን አንዱ ነው፡፡ ግዮን ደግሞ የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል፤ ከሰከላ ማህጸንም ይፈልቃል፡፡ “ሰከላ ዓባይን ወለደች” እንዳለ አቀንቃኙ፡፡

ዓለም ስለዚህ ወንዝ ከበቂ በላይ መረጃ አለው፡፡ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ ዓለም ስለዓባይ የዘነጋው ግን አንድ ነገር አለ፡፡ እርሱም ለብዙ ጊዜ ቅዱሱ ወንዝ ዓባይ ከየት እንደሚነሳ አምኖ ለመቀበል መቸገሩ ነበር፡፡ 6 ሺህ 650 ኪሎ ሜትር እርዝመት ያለው የዓለማችን መለሎ ወንዝ 11 ሀገራትን አቆራርጦ ሜዲትራኒያን ባህር ይገባል፡፡ የዚህ ሚስጥራዊ ወንዝ መነሻ ግን “ወላዲተ ዓባይ” የሚሏት ሰከላ ናት፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መጽሃፈ ሰዋሰው ወግስ፤ ወመዝገበ ቃላት ሀዲስ” በሚል ርእስ 1929 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሃፋቸው በኦሪት ግዮን እና ኤፌሶን የሚል መጠሪያ የነበራቸው ወንዞች ጥቁር ዓባይ እና ነጭ ዓባይ ናቸው ይሉናል፡፡ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ የዓለም አሳሾች የዚህን ወንዝ መነሻ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት ሁሉ አልተሳካም ነበር፡፡

ከፓድሬ ፔሬዝ እስከ ሳሙኤል ቤከር፤ ከሪቻርድ በርተን እስከ ጆን ሀኒንግ ስፔክ ከአራተኛው እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዓባይን ወንዝ መነሻን ለማወቅ የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ምንጩን የሚያመላክቱ አልነበሩም፡፡ በመጨረሻ ግን ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ ከካይሮ እስከ ጣና ተጉዞ የዓባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ፈር ቀደደ፡፡ 1937 እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት ጀርመናዊው ቡክሀርት ባልደክኼር የዓባይ ምንጭ ከኢትዮጵያ ተራሮች ስር ይገኛል ሲል ምስክርነቱን ለዓለም ሰጠ፡፡

ዓባይ እንደ ብርቅ ልጅ ከጥንት እስከ ዛሬ ከውጭ እስከ ውስጥ መጠሪያ ሥሙ ብዙ ነው፡፡ ግዮን ግን የዓባይ ወንዝ የመጽሃፍ ስም ነው፡፡ ምዕራባዊያን ናይል የሚል መጠሪያ የሰጡትን ወንዝ ኢትዮጵያዊያን ስሙን ከግብሩ ጋር ሲያስተሳስሩ ደግሞ ግሽ ዓባይ ይሉታል፡፡ ግሽ ዓባይ የሚለው መጠሪያው ከጻዲቁ አባት አቡነ ዘርዓ ብሩክ ጋር ይተሳሰራል ያሉን የደብረ ፀሐይ ግሽ ዓባይ ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ፀሐይ መምህር ይባቤ ደሳለው ናቸው፡፡

ለሰው ልጅ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ንቃተ ህሊና መሻሻል ምክንያቱ የዓባይ ወንዝ ሸለቆን ተከትለው የሰፈሩ ጥንታዊ ሕዝቦች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ዓባይ ወንዝ ብቻ አይደለም የሚሉት መምህር ይባቤ ታሪክን ከሃይማኖት፤ ጸጋን ከበረከት ጋር አጣምሮ የያዘ ቅዱስ ወንዝ ነው ይሉናል፡፡ ከምድራዊ ዓለም እስከ ሰማያዊው ዓለም ድረስ የዓባይ ወንዝ በረከት ሰፊ ነው የሚሉት መምህሩ፤ በመንፈሳዊ እይታ ገነትን እንዲያጠጡ ከታዘዙት አራት ወንዞች መካከል ግዮን አንዱ ነው፤ በምድራዊው ደግሞ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ በርሃውን ገነት አድርጎ ያልፋል ይላሉ፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ ዓለም ያለውን የተሳሳተ እይታ እና ትርክት ለማረም ከባለቤቶቹ ከእኛ ትጋትን ይጠይቃል የሚሉት መላከ ፀሐይ መምህር ይባቤ ከግድብ ያለፈ ሀገራዊ ትርጉም እና ፋይዳ ለማምጣት የግዮን በዓል እየተከበረ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል ግዮን የወንዝ ቅዱስ የሀገር ንጉስ እንደሆነ የሚያስተምር ነው ተብሏል፡፡ የአንድ ሕዝብ እና ሀገር አስተሳሰብ የሚቃኘው በጊዜ ሂደት በሚፈጠር ልምምድ ነው፡፡ የግዮን በዓልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነትን የሚያገኝ በዓል እስኪሆን ድረስ መስራት ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡

የግዮን በዓል ከጻዲቁ አባት አቡነ ዘርዓ ብሩክ እረፍት ጋር ተያይዞ የሚከበር በዓል ነው የሚሉት መምህር ይባቤ ፤ ይኽም ታሪክን ከሃይማኖት፤ ጸጋን ከበረከት ጋር አስተሳስሮ ለመቀበል ስለሚያስችል ነው ብለውናል፡፡ ዓባይ አደራ የሚያወጣ ታላቅ ወንዝ ስለመሆኑ ምስክሩ ለ30 ዓመታት በአካባቢው ያስተማሩት እና የጸለዩት ጻዲቁ አባታችን ናቸው፤ ለዚያም ግሽ ዓባይ የሚል ሥያሜ ሰጥተውት አልፈዋል ብለውናል፡፡

የግዮንን በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስነት እስኪመዘገብ እና የዓለም ሕዝብ ቅርስ እስኪሆን ድረስ እንሠራለን ያሉት መምህር ይባቤ መንግሥት እንዲያሟላልን የጠየቅናቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ምላሽ እያገኙ ነው ብለዋል፡፡ የግል ባለሃብቶች ወደ አካባቢው በመምጣት ለቱሪስት የሚሆኑ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ሊያሟሉ ይገባል፤ ይኽን ታሪካዊ እና መንፈሳዊ አካባቢን ለማስተዋወቅ እና ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ዘላቂ ድጋፍ እና ክትትል ያስፈልጋልም ብለዋል መምህሩ በመልዕክታቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!