ግዮን የአንድነታችን ገመድ ነው፡፡

107

ባሕር ዳር: ጥር 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 5ኛው የግዮን በዓልና የፃድቁ አቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ ሰከላ ግሽ ዓባይ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በዓሉ በየዓመቱ በዚህ መልኩ መከበሩ በሕዝቦች መካካል መተሳሰብን፣ አንድነትን ፍቅርን እንዲኹም የኔነት ስሜት ፈጥሯል ያሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የቅርስ መምህሩ እንዳላመው ክንዴ ናቸው፡፡

መምህር እንዳላማው ሠከላ ወረዳ “የቱሪዝም እምቅ ሀብቶች፣ ተግዳሮቶች እና የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

መምህር እንዳላው ግዮን የአንድነታችን ገመድ ነው፡፡ ጊዮን ያስተሳሰረው ፍቅር አይፈታም፣ ግዮን የጠራው እንግድነትን አክብሮ ይመጣል እንጅ ጠሪን አያሳፍርም ኹሉም በግሺ ዓባይ ተገኝቶ ሀገሩን አይቷል፤ መነሻውን ተገንዝቧል ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የመጣው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በቁጥር እጥፍ ኾኗል፡፡ ይኽም ግዮን አንድነትን በመስበኩ ነው፣ ኹሉም ፊቱን ለማዞሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የጻድቁ የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ዓመታዊ በዓል ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይከበር እንደነበር የጠቀሱት አቶ እንዳላማው አሁን በዚህ መልኩ መከበሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሌላው ዓለም ጋር እንዲተዋወቅ እድል ፈጥሮለታል ብለዋል፡፡

ግዮን ወንዝ ብቻ አይደለም አንድነት ነው፣ ሕብረት ነው፣ ፍቅር ነው፣ መተሳሰብ ነው ብለዋል፡፡ ግዮንን ማልማት ኢትዮጵያን ማልማት ነው፡፡ ግዮን ለኢትዮጵያ የአይኗ ማረፊያ የልቧ መጽናኛ ተስፋዋም ነው ብለዋል መምህሩ፡፡

የግዮን ወንዝ እና የጻዲቁ የአቡነ ዘርዓብሩክ ቤተክርስቲያንን የሚጎበኙ የሀገር ውስጥም ኾኑ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ባለፉት አምስት ዓመታት ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል፡፡ የቦታው አለመልማት እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ውሎ አድሮ የሚጎበኝ ሰው ቁጥር አናሳ መኾኑን መካድ አይቻልም ብለዋል፡፡

ግዮን ወንዝ የአንድነታችን ገመድ ነው። በግዮን ሥም የተቋቋመው ግሺ ዓባይ የወጣቶች ማኅበር ከአቡነዘርዓ ብሩክ ቤተክርስቲያን በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ቤተክርስቲያኖችን ማስገንባት ችሏል፣ ይኽ ሕብረት ሌሎች ታሪኮችን ይሠራል ብለዋል፡፡
የግዮን እና የጻድቁ የአቡነ ዘርዓብሩክ በዓል በየዓመቱ መከበሩ የዓለም ሕዝብ ዓባይ የማን ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሠጣል ብለዋል፡፡ ግዮን ለዓለም የውኃ ፖለቲካ መነሻ ኾኖ ነበር ያሉት መምህሩ ኹሉም ዓባይን ወይም ግዮንን እንዲያውቀው በር ከፍቷል። ዓይኖች ኹሉ ወደ ዓባይ ዞረዋል፤ በርካቶች ቦታውን ለማየት እየነጎዱም ነው ይኽን ያየ ይመሠክራል ብለዋል፡፡

ዓባይ መተኪያ የሌለው ሀብታችን ነው ተግዳሮቱ እንዲነቀልለት ኑ እዩት ተብሎ በመጠራቱ የመንግሥት አካላት፣ ግለሰቦች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል፣ ስለ ዓባይም በጋራ መክረዋል፣ ምክራቸውን ለማስፈጸም በጋራ አቅደዋል ነው ያሉት፡፡

ዓባይ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ መስተጋብሩ አድጓል ያሉት አቶ እንዳላማው በቀጣይ ከዚህ በላይ መወያየት፣ መረዳዳትና መተጋገዝን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የዓባይ ተግዳሮቶች ብዙ ናቸው ያሉት መምህሩ አንዱ እና ዋነኛው የተፈጥሮ ሀብቱ መመናመን በመኾኑ ይኽንን ለመቀየር የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ4ኛው ዙር የግዮን በዓል ላይ የተሠጠውን ኀላፊነት ተቀብሎ በአራት ዲፓርትመንት አዋቅሮ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ፖሊሲ እንዲወጣ፣ እንዲተገበር መደረጉም አንዱ የበዓሉ ልማት ነው ብለዋል መምህሩ፡፡ ግዮን ሊለማ ነው፡፡ በአካባቢው ተወላጆች አስተባባሪነት የቦታ መከለል፣ ማስጠበቅ እና ችግኝ ማልማት የቀጣይ አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል መምህር እንዳላማው፡፡

አቶ እንዳላማው እንዳሉት ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ 28 ምሁራን በማሳተፍ ቅርሶችን ሲያጠና መቆየቱን ገልጸው በጥናቱም በርካታ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ ተግባራት ይፈጸማሉ፤ ዓባይ ይለማል የዓለምም ሀብት ይኾናል፣ የዓለም ዓይኖች ወደ ዓባይ የሚያዩበት ጊዜ ደርሷል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ :- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!