ግንባር በመሰለፍ የህይወት መሰዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸውን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

0
39

ግንባር በመሰለፍ የህይወት መሰዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸውን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር:ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኀይል፣ ለሚሊሻ እና ለፋኖ አባላት አጋርነታቸውን ለማሳየት ”ደማችንን በደም ዋጋ ለወደዱን ለመከላከያ ሠራዊት እና ለልዩ ኀይሎቻችን” በሚል መሪ መልዕክት ደም ለግሠዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባው ጌቴ እንዳሉት የቢሮው ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች ለህልውና ዘመቻው ደም በመለገስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ አቶ አበባው አሸባሪው ትህነግ ሀገር ለማፍረስ በፈጸመው ወረራ በመጀመሪያ ጉዳት የሚደርሠው በኢኮኖሚው ላይ ነው፤ ኢኮኖሚውን ከውድቀት ለመታደግ ደግሞ ግብርና ድርብ ኀላፊነት አለበት፤ ይህን ኀላፊነት ለመወጣት ጠንክሮ እየሠራ እንደኾነም ነው ያስረዱት፡፡ የቢሮው ሠራተኞች የችግሩን ግዝፈት ታሳቢ በማድረግ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ያለውን ባለሙያ እያስተባበሩ ወደ ግንባር የሄደው ሚሊሻ እና ፋኖ ማሳ ጦም እንዳያድር እየሠሩ እንደኾነ ነው አቶ አበባው የነገሩን፡፡

ቀበሌ እና ወረዳ ላይ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ደም ከመለገስ እና የወር ደመወዛቸውን ከመስጠት ባሻገር የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ ነው፤ የህልውና ዘመቻውን በአሸናፊነት ለመወጣት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ምክትል ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ሀገር ለማፍረስ ሲጥር በዝምታ ማለፍ አይቻልም፤ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዳግም እንዳይመለስ ለማድረግ ጠንክሮ በመሥራት ግንባር ለተሠለፈው ኃይል የኋላ ደጀን መኾን ያስፈልጋል ብለዋል አቶ አባበው፡፡ ”ለዚህ ደግሞ የወር ደሞዛችንን ሰጥተናል፤ ሠራተኞቻችን በስንቅ ዝግጅት እንዲሳተፉ አድርገናል፤ ደምም ለግሰዋል” ብለዋል፡፡

በግብርና ቢሮ የእቅድና በጀት ባለሙያው አቶ አለማየሁ እንደሻው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እንዲሁም ፋኖ የሀገሩን ህልውና ለማስጠበቅ ህይወቱን እየገበረ ነው ብለዋል፡፡ ደም በመለገስ ለሠራዊቱ ያለኝን አጋርነት በማሳየቴ የህሊና እርካታ ሠጥቶኛል ነው ያሉት፡፡ ደም ከመለገስ ባሻገር በግንባር ለተሠለፈው የመከላከያ ሠራዊት ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ከኋላ በመሰለፍ ደጀንነታቸውን ለማረጋገጥ ማቀዳቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

አቶ አለማየሁ ማኅበረሰቡ የበሬ ወለደ ወሬን ወደጎን በመተው አጋርነቱን ማሳየት አለበትም ብለዋል፡፡ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ ወሬኞችን መስማት ተገቢ አይደለም ነው ያሉት፡፡ አቶ አለማየሁ ”ከችግር መውጫ ቁልፉ አንድነት ነው፤ አንድነታችንን አጠንክረን መያዝ ይጠበቅብናል፤ አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለመነጣጠል ቢጥርም እኛ ግን ጀግኖች አባቶቻችን ጣሊያንን ድል ያደረጉበትን አንድነት አጠንክረን መያዝ አለብን” ብለውናል፡፡

ደማቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሠጡት የኦዲት ባለሙያዋ ወይዘሮ የሽ አለሙ ደማቸውን የሰጡት ህይወቱን ሳይሣሣ ለሚሠጣቸው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እንዲሁም ፋኖ አጋርነታቸውን ለማረጋገጥ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ ወይዘሮ የሺ ደም ከመለገስ ባሻገር ስንቅ በማዘጋጀት እና በማስተባበር እየተሳተፉ ነው፤ በግንባር የተሠለፈው ሠራዊት በድል እንዲመለስ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፣ ሽንፈት ለኢትዮጵያውያን ሞት ነው፤ ለዚህ ደግሞ በርካታ ማሳያዎች አሉ፤ ጠላት ሁል ጊዜም በወሬ ለማሸነፍ ቢጥርም አይሳካለትም፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ የአባቶችን ጀብድ በመድገም በድል ይመለሳሉ ሕዝቡም በማንኛውም አግባብ ከጎናቸው ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here