ግሽ ዓባይ የግዮንን በዓል ለማክበር ዝግጅቷን አጠናቃለች።

0
79

ጥር 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የግዮንን በዓል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሰከላ ወረዳ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አስታወቀ።

ሰከላ ከባሕር ዳር ከተማ በ164 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ወረዳዋ የታላቁ የዓባይ ወንዝ መነሻ ናት፡፡ ወረዳዋን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረክ በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ ነግረውናል፡፡ በዓሉን ለማክበር የአገው የፈረሰኞችን ማኅበርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ ጎብኝዎች፣ ዳያስፖራዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሰከላ ወረዳ ተወላጆች ይታደማሉ።

በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግዮን በዓል ነገ ጥር 13/2014 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ያሉት ኀላፊው በበዓሉ ላይ ሲምፖዚየም፣ የፈረስ ጉግስ፣ ዓባይን ከምንጩ ለማልማት ምን መደረግ አለበት በሚል ርእስም ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

የሰከላ ወረዳ መናገሻ ግሽ ዓባይ ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለሙ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ኀላፊው ገልጸዋል። የወረዳው የእደ ጥበብ ምርቶች ለገበያ ይቀርባሉ፤ የፈረስ ጉግስ፣ የገና ጨዋታ የበዓሉ ድምቀት ናቸው ብለዋል፡፡

ወረዳዋ የዓባይ ወንዝ መነሻ የግሼ ተራራ፣ የፋሲል ግንብ (ፋሲል ጎንደር ከመግባቱ በፊት የገነባው)፣ የጉደራ ሐይቅ፣ የዓላዛር ዋሻ ፣ ድንጋይ ቀዳዳ እና የሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ባለቤት በመሆኗ ወረዳዋን ለማስተዋወቅ በዓሉ መከበሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት፡፡

በየዓመቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ወረዳዋን ይጎበኛል፤ ይህን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ በማድረግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መነሻ ለማስተዋወቅና የዓባይ ወንዝ መነሻ የት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል አቶ ዘመኑ፡፡ የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ግሽ ዓባይ ከተማ የሚከበረው የግዮን በዓል ዓባይን ከምንጩ ለማልማት እና ቦታውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ቦታውን በማልማት ራሳቸውን በመጥቀም ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/