ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት የያዘው አቋም በቆየው መዋቅራዊ አደረጃጀት ከሆነ ውጤታማነቱ እንደሚያጠራጥር የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ተናገሩ፡፡

0
98

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2012 ዓ/ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የ2012 በጀት ዓመት ከመንግሥት ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ ማድረግ አንዱ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዝዳንቷ በምግብ ሸቀጦችና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚታየውን ሕገ ወጥ አሠራር መቅረፍ የሚያስችል ሥራ መፍጠር የበጀት ዓመቱ ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ለመሆኑ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመከላከል መንግሥት ይፋ ያደረገው ጉዳይ ምን ያክል ውጤታማ ሊሆን ይችላል? በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር ታደሰ መንግሥቴ (ዶክተር) በጉዳዩ ዙሪያ ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዶክተር ታደሰ እንደሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ ፕሬዝዳንቷ በመክፈቻ ንግግራቸው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግሥት በዓመቱ ያቀደውን ሥራ በተመለከተ ያቀረቡት ጥቅል ሐሳብ ነው፡፡ የገበያ አለመረጋጋት ሲከሰትና የዋጋ ንረቱ ሲያሻቅብ ድርጊቱን ለማስቆም ከዚህ በፊት ሲነገር ከነበረው ሐሳብም የተለየ ነገር የለውም፡፡ በእርግጥ በቀረበው ሪፖርት የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርናው መስክ የምርት ዕድገት ማሳዬቱ ተነግሯል፤ የያዝነው ዓመት የምርት ዘመን የምርት ውጤትም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ እንዲሆን ለአርሶ አደሩ በቂ ግብዓት መሠራጨቱን ፕሬዝዳንቷ አቅርበዋል፤ የዋጋ ንረቱ ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

እንደ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ስኳርና መሰል ሸቀጦች የዋጋ መውጣትና መውረድ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ግለሰቦች የኑሮ ዑደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው፡፡ ዶክተር ታደሰ እንደሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ  በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት ሊከሰት የሚችለው ዋናው ጉዳይ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ሲኖር ነው፡፡ ፍላጎትን ማስተናገድ የሚያስችል የምርት አቅርቦት ከሌለ ሸማቾች በውስን ምርቶች ላይ እንዲረባረቡ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በአንጻሩ የሸቀጦች ዋጋ ተመን ሊያሻቅብ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖርም እሙን ነው ፡፡

‹‹ያለፈው ዓመት የምርት ዘመን ጭማሪ አሳይቷል›› የሚለው ድምዳሜ የመንግሥት አቋም ቢሆንም ነባራዊ የገበያ ሁኔታው የሚያሳየው የቀረበው ሐሳብ ከሪፖርት የዘለለ አለመሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ምርት በበዛበት ጊዜ ሁሉ ገበያው ራሱን ከፍላጎት ጋር አጣጥሞ መምራት እንደሚችልም ሙያዊ ዕይታቸውን በማስረጃነት አስቀምጠዋል፡፡ ምናልባትም የምረት ጭማሪ ነበር የሚለው ጉዳይ ትክክል ቢሆንም ሕጋዊ እርምጃ የሚያስፈልጋቸው ሕገ ወጥ ተግባራት ሲሠሩ የነበሩ በመሆኑ አፅንኦት ተሰጥቶት ሊብራራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ ለዋጋ ንረቱ መባባስ እጃቸው አሉባቸው ያሏቸው ኮንትሮባንዲስቶችና ሌሎች በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩትን ወደ ሕጋዊ የንግድ መረብ እንዲገቡ ማድረግ ተብሎ የተነሳው ሐሳብ ጥሩ እንደሆነና  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ንግድ ፈቃድና በሚታወቅ ንግድ ቦታ እየሠሩ ምርት የሚከዝኑና መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚደርጉት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ጉዳይ ትኩረት ካልተሰጠው መንግሥት በበጀት ዓመቱ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል የያዘውን አቋም መፈታተኑ እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡

ገበያውን ለማረጋጋትም ሆነ ንረቱን ለመቆጣጠር መንግሥት የያዘው አቋም ከቀበሌ ጀምሮ ባለው መዋቅራዊ አደረጃጀትና በተለመደው የመንግሥት አሠራር ከሆነ ስኬታማነቱ አጠራጣሪ መሆኑንም ዶክተር ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለው የመንግሥት መዋቅር ንረቱን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ ተቋም የለም›› የሚል ሐሳብ ነው ምሁሩ ያላቸው፡፡ ተግባሩ እየተከወነ ያለው በዘመቻ ሥራ ወይም በኮሚቴ ሲያልፍም በግብረ ኃይል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ኃላፊነት ስለሚጠይቅ ተግባሩን በወቅቱ ተከታትሎ ውጤት ላይ ለማድረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ነው ያብራሩት፡፡

በሀገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይ የኑሮ ውድነትን ለመዋጋት መንግሥት ያስቀመጠው ግብ ዒላማውን እንዲመታ መደረግ ያለባቸውን ሙያዊ ምክሮችንም ዶክተር ታደሰ አብራርተዋል፡፡ በዋናነትም መንግሥት ከሪፖርት የዘለለ በቂ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መሥራት እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶችም ይሁኑ ከውጭ ሀገራት በድጎማ በሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች ገበያው ሙሉ የሚሆንበት ዕድል መፈጠር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳለጥም ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሕጋዊ ሽፋን አስካላቸው አካላት ድረስ ያለውን ሰንሰለት መበጠስ የሚያስችል አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የተሻለ ምርት ካለባቸው አካባቢዎች ዝቅተኛ አቅርቦት ወዳለባቸው ቦታዎች ምርት እንዲኖር የሚሠሩ አምራቾችና አቅራቢዎች የሚበረታቱበት አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የዋጋ ንረቱን የመከላከል ተግባር የመንግሥት ብቻ ባለመሆኑ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ቁርጠኛ ተግባርም መሠራት ያለበት መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የዋጋ ንረቱን ለመከላከል የተሻለ አመለካከትና የተቆርቋሪነት ስሜት ያለው የነቃ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀት እንዲኖር መሥራትም ሌላኛው የመፍትሔ ሐሳብ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ በሕገ ወጦች ላይ ፈጥነው እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ የመንግሥት አካላትና ሥርዓት አስከባሪዎች ሊኖሩ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የሀገሪቱ የሠላምና የፀጥታ ሁኔታ ሌላኛው ንረቱን የመከላከል ሂደት ፈተና ሊሆን ስለሚችልም ለሠላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ምሁሩ መክረዋል፡፡

የሀገሪቱ ነባራዊ የሠላም ሁኔታ መሻሻል ካልቻለ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት ማድረሱ ስለማይቀር ለሠላም ሁሉም ሰው ዘብ መቆም እንዳለበትም መክረዋል፡፡ አምራቾችና አቅራቢዎች እንዲሁም ንረቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ተረጋግተው ሊሠሩ የሚችሉት ሕግና ሥርዓት ሲከበር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here