“ጁንታው በእስር ቤት በሰለጠኑ ውሾች እስከማስነከስ ግፍ ፈጽሞብናል” የኮረም ከተማ ነዋሪዎች

0
354

“ጁንታው በእስር ቤት በሰለጠኑ ውሾች እስከማስነከስ ግፍ ፈጽሞብናል” የኮረም ከተማ ነዋሪዎች

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) ”የህወሃት ጁንታው ቡድን ማንነትን መሰረት በማድረግ ብቻ በእስር ቤት ውስጥ በሰለጠኑ ውሾች እስከማስነከስ ግፍ ፈጽሞብናል ሲሉ የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጁንታው ከተወገደ ወዲህ የኮረም ከተማ ወደቀደመ አንጻራዊ ሰላሟ እየተመለሰች መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ እክያው ተመስገን እንደገለጹት የህወሃት የጥፋት ቡድን የሰው ልጅ ይፈፅመዋል የማይባለውን በደል ሲፈፅም ቆይቷል።
ቡድኑ ባለፉት 30 ዓመታት የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው የታፈነበት አስቸጋሪ ወቅት እንደነበረም ጠቅሰዋል።
“ማንነታችንን መሰረት በማድረግ ብቻ ድብደባና እስር ይደርስብን ነበር” ያሉት አቶ እክያው በፖሊስ ጣቢያ ታስረው በሰለጠኑ ውሾች ያስነክሷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
ሌሎች ከሃምሳ በላይ ሰዎችም በውሻ እንዲነከሱ ተደርገው ተመሳሳይ ግፍ እንደተፈጸመባቸው አመልክተዋል።
”በእኔ ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ግፍና በደል መቋቋም ያልቻሉ ልጆቼ ከተማውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ኑሯቸውን እንዲገፉ ተገደዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የክህደት ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ኮረም ከተማ ከጁንታው አገዛዝ ነጻ በመውጣት ወደ ቀደመ አንጻራዊ ሰላሟ እየተመለሰች መሆኑንም ገልጸዋል።
“ባለፉት 30 ዓመት የኦፍላ ወረዳና የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ማንነትን መሰረት በማድረግ በሚፈጸም ግፍና በደል ተሳቀው ቀያቸውን ለቀው ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በመሄድ እንዲኖሩ ተገደዋል” ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ሃይሉ ተስፋዬ ናቸው።
ቡድኑ በገዛባቸው ዓመታት በኮረም ከተማ በመሰረተ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልነበረች የገለጹት አቶ ሀይሉ፤ በአካባቢው ለችቡድ ፋብሪካ ማምረቻ በቂ ግብዓት እያለ ፋብሪካው ሌላ አካባቢ እንዲቋቋም እሰከ ማድረግ አስከፊ ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰዋል።
“የከተማው ወጣትም የስራ እድል ሳይፈጠርለት ቆይቷል” ያሉት አቶ ሀይሉ አሁን በመጣው ለውጥ ትልቁ ተቋዳሽ ወጣቱ እንደሚሆን አመላክተዋል።
“የሃገር መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል ጁንታው ላይ በወሰዱት ህግ የማስከበር ርምጃ ለኦፍላ ወረዳና ለኮረም ከተማ ነዋሪዎች ትልቅ ተስፋን ፈንጥቋል” ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ላይ አካባቢው ወደ ቀደመው ሰላሙ መመለሱን አመልክተዋል።
ወጣት በርሄ ማርየ በበኩሉ ህወሃትን የሚቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ድጋፍ አድርገሃል በሚል ለስድስት ዓመታት በማረሚያ ቤት ታስሮ በደል እንደደረሰበት ተናግሯል፡፡
“ከእስር ከወጣሁ በኋላም ወንጀል ፈጽመሀል በሚል የስራ ፈጠራ የገንዘብ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆን ተደርጊያለሁ” ብሏል።
አሁን ላይ በመጣው ለውጥ ደስተኛ መሆኑንና ለውጡ ለወጣቶች ሰርቶ ለመለወጥ ትልቅ አስተዋጾ እንዳለው ወጣት በርሄ ገልጿል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ