ድጋሜ ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምሕርት መምሪያ አስታወቀ።

0
65

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በበርካታ ትምሕርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ ተቋርጦ ነበር፤ ያልተቋረጠባቸው አካባቢዎችም ቢኾኑ የሥነ ልቦና ጫናው በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በዚህ ምክንያት የዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ያላመጡት ተማሪዎች ፈተናውን በድጋሜ እንዲወስዱ መወሰኑ ይታወሳል።
በቀጣይ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተገቢውን ዝግጅት መደረጉን ያነጋገርናቸው ተፈታኝ ተማሪዎችና የትምሕርት ባለሙያዎች ነግረውናል።
ተማሪ ዳኘው ወዳጅ በወገራ ወረዳ አምባ ጊዮርጊስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ተፈታኝ ነው። ተማሪ ዳኘው እንደነገረን እንደማንኛውም የገጠር ተማሪ በእግሩ በመጓዝ ትምሕርቱን ተከታትሏል። ከትምሕርት መልስ ደግሞ አኹንም ለሰዓታት ተጉዞ ቤተሰቦቹን ያግዝ ነበር። በዚህ ኹኔታ ውስጥ ኾኖ 10ኛ ክፍል ሦስት ነጥብ፣ በክፍል ውስጥ ደግሞ እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ ነበር እየያዘ አስራ ሁለተኛ ክፍል የደረሰው።
ይኹን እንጅ ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና የጸጥታ ችግር ምክንያት የከፍተኛ የትምሕርት መግቢያ ውጤት ማምጣት አልቻለም። በዚህ ከፍተኛ ቁጭት ያደረበት ተማሪ ዳኘው በመንግሥት የተሰጠውን ዳግም የመፈተን እድል ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አጫውቶናል። ተማሪ ዳኘው አኹን ላይ ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ትምሕርቱን እየተከታተለ ነው። ከትምሕርት መልስ ለአራት ሰዓታት ያነባል።
መምሕራን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምሕት ተቋርጦ በነበረበት ወቅት ያልተዳሰሱ ይዘቶችን በመሸፈንና ያለፉ ዓመታት ጥያቄዎችን በመሥራት እያገዟቸው መኾኑን ገልጾልናል። ቤተ መጽሐፍት የእረፍት ቀናትን ጨምሮ እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ክፍት መደረጉን ተናግሯል።
መምሕር አሸናፊ አበበ በባለፈው ዓመት የከፍተኛ የትምሕርት መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ትምሕርት እየሰጡ እንደሚገኙ ነግረውናል። የ2013 ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መኾን በፈጠረባቸው ቁጭት በክረምትም ጭምር ለማስተማር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የአምባጊዮርጊስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ርእሰ መምሕር ካሳሁን ንጉሴ ድጋሜ ተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች ጋር በተደረሰ ስምምነት ከመደበኛ ተፈታኝ ተማሪዎች ጋር እንዲማሩ መደረጉን ነው ያነሱት። የባለፈውን ዓመት ውጤት ለማካካስ መምሕራን ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ተደርጓል። አስፈላጊ የኾኑ መጽሐፍትን መሟላታቸውንም ነግረውናል።
የወገራ ወረዳ ትምሕርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርሃኑ መኮንን እንዳሉት በ2013 ዓ.ም በወረዳው ከተፈተኑት ተማሪዎች ውስጥ ከ740 በላይ ተማሪዎች ውጤት ያላመጡ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ከ560 በላይ ተማሪዎች ድጋሜ ለመፈተን መመዝገባቸውን ነግረውናል። አኹንም ያልተመዘገቡ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ጥሪ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምሕርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ እንዳሉት
በ2013 ዓ.ም ተፈታኝ ተማሪዎች በነበረው የዝግጅት እና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ከዚህ በፊት በዞኑ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የውጤት መቀነስ ታይቷል።
የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄም የ2013 ዓ.ም ተፈታኞች ድጋሜ እንዲፈተኑ መወሰኑን ተከትሎ ዞኑ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አቶ ክንዱ ነግረውናል።
የተደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች፦
•ለዳግም ተፈታኝ ተማሪዎች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል።
•የተመረጡ መጽሐፍት እንዲሟሉ ተደርጓል።
•ቤተ መጽሐፍትም የእረፍት ቀናትን ጨምሮ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ክፍት ኾነው እንዲያገለግሉ ተደርጓል፤
•የትምሕርት ዓይነቶች ቀድመው እንዲሸፈኑ ተደርጓል፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተዘለሉ የታች ክፍሎች የትምሕርት ይዘቶች የክለሳ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
•በኹሉም የትምህርት ዓይነቶች ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ጥያቄዎችን በማውጣት እንዲሠሩ ተደርጓል።
•ያለፉ ዓመታት ጥያቄዎችን በመሥራት ተማሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
•ተማሪዎችን በጥናት ቡድን በማደራጀት በየችሎታቸው እንዲተጋገዙ እየተደረገ ነው።
•በክረምት ለሚሰጠው ትምሕርት እና ተማሪዎች ያስቀመጡት ግብ እንዲሳካ ትምሕርት ቤቶች ከወላጆች ጋር ጭምር ውል እንዲወስዱ ተደርጓል።
•በዞኑ የሚገኙ አስፈታኝ ትምሕር ቤቶች የጥያቄና መልስ ውድድር አካሂደዋል። ከሰኔ 30 በኋላም ተማሪዎች በመረጡት መምሕር እንዲማሩ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በዞኑ ከ12 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎች ድጋሜ ፈተና ይወስዳሉ፤ እስከ አኹንም 75 በመቶ ተመዝግበዋል። እስከ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ተመዝግበው በክረምቱ ወራት የማይማሩ ተፈታኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው ፈተና ላይ እንደማይቀመጡ ተረድተው በቀሪው ጊዜ ፈጥነው እንዲመዘገቡ ምክትል ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል። ወላጆችም ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/