ዳዳብ በተባለ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ድጋፍ ጠየቁ፡፡

176

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜናዊ ኬንያ ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ እስከ 30 ዓመታት የቆዩት 4 ሺህ 500 ያህል ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡

በኬንያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ተወካዮች እና በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ትናንት ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ዳዳብ ውስጥ ከስደተኞች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም ኢትዮጵውያኑ ወደ ሀገራቸው በመመለስ እንደሌሎች ወገኖቻቸው ህይወታቸውን መምራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

እስከ 30 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በስደተኛ መጠለያ ውስጥ የቆዩት 4 ሺህ 500 ያህል ስደተኞች መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ባለስልጣን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል። አብዛኛዎቹ ስደተኞች ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌ እና ከጋምቤላ ክልሎች የሄዱ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ምክትል ኃላፊ ዎልፑርጋ ኢንግፕሬክት ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው መንግስት ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለማስገባት የሚቻለውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ በአሁኑ ወቅት ከ200 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኙበታል፡፡