ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር፤ በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ለገበታ ለትውልድ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፡፡ በቅርቡ ይፋ ስለተደረገው ገበታ ለትውልድ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ እና በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከዚህ ቀደም ለቀረቡት ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪዎች የዕውቀትና የገንዘብ ድጋፎችን በማድረግ ለፈጸሙት ታሪካዊ ገድል የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት የቀረበውን “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪ በመቀበል እንደወትሮው ድጋፍ እንዲያደርጉ ክቡር አምባሳደሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የተጀመረውን የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ ሚሲዮኑ ከሁሉም የማኅበረሰቡ አደረጃጀቶችና የሚዲያ አካላት ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ማኅበረሰብ ሊያሳትፉ የሚያስችሉ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ማዕከላት የንቅናቄ መድረኮችን እንደሚያካሄድ ጠቁመዋል፡፡
ሚሲዮኑ በደቡበ አፍሪካ እና በሚሸፍናቸው የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን የሚመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ኤምባሲው አስታውቋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!