ዳሽን ባንክ የ”ዱቤ አለ” አገልግሎትን በደብረብርሃን ከተማ ለንግዱ ማሕበረሰብ እያስተዋወቀ ነው።

82
ደብረ ብርሃን:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ዱቤ አለ” ዳሽን ባንክ ከኤግል ላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ያቀረበው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ፤ ሸማቾችን ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር የፈለጉትን ምርት ዛሬ በዱቤ ገዝተው ነገ የሚከፍሉበት አገልግሎት ነው።
በባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ ፈይሰል አብዱ እንዳሉት ዳሽን ባንክ በባንክ ኢንዱስትሪው አዳዲስ አሠራሮችን እያስተዋወቀ ነው። ከዚህ ውስጥ የዱቤ አገልግሎት አንዱ ሲኾን ባንኩን ከደንበኞች ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስር ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት እንደኾነም አመላክተዋል።
ዳሽን ባንክ ዱቤን በቴክኖሎጅ ከማዘመን ባሻገር በሸማቾች እና በንግድ ተቋማት መካከል መተማመን በመፍጠር ሸማቾች ፍላጎታቸውን በጊዜ እንዲያሟሉ፣ አምራቾች እና አገልግሎት አቅራቢዎች ደግሞ ሽያጫቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መካከል ግብይትን ማቀላጠፍ፣ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የብድር ተጠቃሚ ማድረግ፣ ምርትና አገልግሎትን በመተግበሪያ ማስተዋወቅ፣ ብዙ አይነት ምርትና አገልግሎቶችን መሸጥ ማስቻል እና ሽያጭን ማሳደግ ይጠቀሳሉ።
እስከ 700 ሺህ ብር የሚደርስ የዱቤ አገልግሎት እንደሚሠጥም ነው አቶ ፈይሰል ያስገነዘቡት።
በዚህ የትውውቅ መድረክ ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ከንግዱ ማኀበረሰብ የተውጣጡ ነጋዴዎች እና አገልግሎት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!