“ዲጂታል ሚዲያዎች የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተከትለው መሥራት ይጠበቅባቸዋል” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት

22
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዲጂታል ሚዲያዎች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሳይሆን የሀገርንና የሕዝብን ሰላም መሰረት ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ገለጸ። የሀሰት መረጃዎችን፣ ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ ምክር ቤቱ ትናንት ባዘጋጀው የበይነ መረብ ሥነ ምግባር ደንብ ሥልጠና መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ በዲጅታል ሚዲያው በሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች ፣ የጥላቻ እና ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የማስተላለፍ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ዲጂታል ሚዲያው ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ መሥራት ካልቻለ በሀገር ደኅንነትና በሕዝብ ሰላም ላይ ስጋት ስለሚፈጥር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትም ዲጂታል ሚዲያዎች የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው እንዲሠሩ የበይነ መረብ የሥነ ምግባር ደንብ አዘጋጅቷል።
ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነትን እንዲጠበቅ መሥራት የሁሉም ሚዲያ ኃላፊነት መኾኑን አመልክተው፤ ዲጂታል ሚዲያው የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር በተከተለ መልኩ መሥራት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ሚዲያ ተደራሽነት እየጨመረ ነው ያሉት አቶ አማረ፤ ዲጂታል ሚዲያዎች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሰላም መሰረት ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው እንዲሠሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባዘጋጀው የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንብ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።
የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር የተከተለ ዲጂታል ሚዲያ በሀገር ግንባታና ለሕዝቡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ በአንጻሩ ሥነ ምግባርን ያልተከተለ፣ ግጭት ቀስቃሽ፤ የሀሰት መረጃዎችንና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ዲጂታል ሚዲያዎች የሕዝብ ሰላምና የሀገር ስጋት መኾናቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ በዲጂታል ሚዲያዎች የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እውቅና የሚያገኙበት አሠራር መዘርጋቱንም ጠቁመው፤ ዲጂታል ሚዲያዎች ለኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ረገድ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ መሥራት አለባቸው ብለዋል። የዲጂታል ሚዲያዎች ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ መልዕክት ከማስተላለፍ ድርጊታቸው ተቆጥበው ሥነ ምግባርን አክብረው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
በበይነ መረብ ጋዜጠኝነት የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ኀይሉ በአብዛኛው በዲጂታል ሚዲያው እየተሳተፈ ያለው ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጪ መኾኑን ጠቁመው፤ የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡ የሚመለከተው በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ኾነው በዲጂታል ሚዲያ ተሳትፎ ያላቸውን ነው ብለዋል። በዲጂታል ሚዲያ የሀሰት መረጃ፣ የጥላቻና የግጭት ጉሰማ መልዕክት የሚያስተላልፉት በሙያው ዕውቀቱና ሥነ ምግባሩ የሌላቸው ግለሰቦች መኾናቸውን ለኅብረተሰቡ ማሳወቅና ማስገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ዛሬ ግለሰቦች በዲጂታል ሚዲያዎች የታዋቂ ሰዎችና የፖለቲከኞችን ስም በመጠቀም የሀሰት መረጃና የጥላቻ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ ያሉት አቶ ታምራት፤ ስለ ዲጂታል ሚዲያዎች በትክክል ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ጠብቀው ከሚሠሩ ሚዲያዎች ይጠበቃል ነው ያሉት። ዘገባው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!