“ደቡብ ሱዳን ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር ትደግፋለች” አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን

161

“ደቡብ ሱዳን ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር ትደግፋለች” አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን

ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደቡብ ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ገለጹ።

አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን እንደገለጹት የዓባይ ውኃ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት በመሆኑ ሁሉም ያለምንም ችግር ሊጠቀምበት ይገባል።

በውኃው ላይ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ልማታዊ ጎናቸው መታየት አለበት ያሉት አምባሳደሩ ችግሮች ካሉም ሀገራቱ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችም በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ሦስቱ ሀገራት ወደ ዘላቂ መፍትሔ መምጣት እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።

የአፍሪካ ሕብረት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ቁመና እያለው ለመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ለሌላ አካል ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ አያስፈልግም ብለዋል።

አፍሪካ ሕብረትም የታዛቢነት ሚና ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመረዳት ሁነኛ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት እንደሚገባው ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

ሕብረቱ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህም እውን ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላም ግንባታ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ ሀገር ናት ያሉት አምባሳደሩ በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ተስፋ ሳትቆርጥ ሀገራቸው አሁን ላለችበት ሰላምና መረጋጋት እንድትደርስ የኢትዮጵያ አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሰላም አዋላጅ ነች” ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአየር፣ የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመክፈትና የማጠናከር ሥራ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል። ይህንንም በተመለከተ ከሚመለከተው ከኢትዮጵያ ተቋምና ከከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአካባቢው ካላት ሚና አኳያ ውስጣዊ ሰላሟን በሟስጠበቅ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ማስተሳሰር ከቻለች ሀገራቱን ወደ ልማትና እድገት የመምራት እድሏ ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m