ግንቦት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መቅድም ታውቅበታለች፣ መብለጥ ትችልበታለች፣ በነጻነት እና በጀግንነት ታሪኳ መላው የጥቁርን ሕዝብ አሰባስባለች፣ አንገት የደፋውን ቀና አድርጋለች፣ ለተጨነቀው ደርሳለች፣ ብርሃን ለጠፋበት ብርሃን አሳይታለች፣ መንገድ ለጠፋው መንገድ መርታለች፣ አፍሪካውያን እንደማይቻሉ፣ ጠላቶቻቸውን እንደሚጥሉ፣ በነጻነት መኖር እንደሚችሉ፣ በክንዷ ነጻነትን አምጥታ፣ ነጻ ኾና አሳይታለች፡፡ በርም ከፍታለች፡፡
እርሷ የአፍሪካ ምልእክት ናት፣ ጥቁሮች የሚኮሩባት፣ መገለጫችን፣ አለኝታችን፣ መመኪያችን የሚሏት፣ እርሷ ጠላት የሚፈራት ሀገር ናት በጥቁሮች ምድር እንዳሻው ሲኾን የነበረውን ጠላት ቀጥተዋለች፣ ወንዜን አትደፈርም ብላ ዶግ አመድ አድርገዋለችና፡፡ ጥቁሮች እስከ ዘላለም በእርሷ ታሪክ ይመካሉ፣ ነጮች እስከ ዘላለም በእርሷ ታሪክ ይቆጫሉ፡፡ ለምን ካሉ በእርሷ ክንድ ተመትተዋል፣ በእርሷ ክንድ በዓለም አደባባይ ተዋርደዋል፣ በእርሷ ክንድ ተቀጥቅጠው ማሩኝ ብለዋልና፡፡
በአሸናፊነት የኖረው የተስፋዋ ምልክት፣ መለያዋና መዋቤዋ ሠንደቋ የአፍሪካን ምድር አዳርሷል፣ ጥቁሮችን አልብሷል፡፡ አፍሪካን ያሰበ ኹሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ይመጣበታል፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ምንጩ ከየት ነው ብሎ የጠየቀ ኹሉ ከአሸናፊዋ ሀገር የመጣ ነው ይባላል፡፡ አሸናፊ ኹልጊዜም ታሪኩ ይወረሳል፣ ኹልጊዜም በጀግንነት ስሙ ይነሳል፡፡ እርሷ በአሸናፊነት የኖረች፣ የነኳትን የቀጣች፣ ወንዝ እንሻገር፣ ወሰን እንድፍር ያሉትን ያንበረከከች፣ አሳፍራ የመለሰች፣ በጠላት ላይ ልቃ የታየች፣ ከፍ ብላ የኖረች ናት፡፡
በግፍ ለተገፉት ድምጽ ናት፣ ለፍትሕ እና ለርትዕ ተከራካሪ ናት፣ ለእውነት፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነት ትልቅ ክብር አላት፡፡ ዓለምን የሚያሰባስበውን፣ የሰውን ልጅ የሚጠቅመውን፣ ፍቅርና አንድነት የሚያመጣውን ኹሉ ትደግፋለች፡፡ የአፍሪካ ምልክት፣ እናትና መመኪያ የኾነችው ኢትዮጵያ ድል አድርጋ ለተጨቆኑት መንገድ ካሳየች በኋላ ዝም አብላ አልተቀመጠችም፡፡
አፍሪካውያን የሚሰበሰቡበትን፣ አንድ የሚኾኑበትን፣ በምድሯ የሚበዛውን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ የሚያውለበልቡበትን መንገድ መክፈት አስፈለጋት፡፡ በአዲሱ መንገድ አፍሪካውያን በጋራ እንደሚደሰቱ አስቀድማ ተረድታለችና፡፡ በአንድ ሜዳ ሥር የአፍሪካ ልጆች የሚሰባሰቡበትን፣ ስለ ፍቅር የሚዘምሩበትን፣ ስለ አንድነት የሚያወሩበትን፣ ስለ ሰላም የሚሰብኩበትን መንገድ ፈለገች፡፡ አፍሪካውን ብቃታቸውን የሚያሳዩበት፣ በጋራ የሚደሰቱበት፣ በአብሮነት የሚፈኩበትን የአፍሪካን ዋንጫ መሠረተች፡፡
ከአንድ ወንዝ ጠጥተው ያደጉትን፣ ታሪካቸውን፣ ስልጣኔያቸውንና ኃያልነታቸውን በአንድ ወንዝ የሚገልጡትን፣ የግዮን (የዓባይን) ልጆች ይዛ የአፍሪካን ዋንጫ መሠረተች፡፡ በዚያ ዘመን ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በዙፋን ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ እርሳቸው የአፍሪካውያን አንድነት ምን ያክል ኃይል እንዳለው ተረድተዋልና ጥሩውን ተግባር ደገፉት፡፡ ሀገራቸው ዓለምን አንድ በሚያደርግ ድርጅቶች መሥራች እንድትኾን አድርገዋል፡፡ ይህችው ቀዳሚ ሀገር የአፍሪካን ዋንጫ መመሥረት ለስሟም፣ ለግብሯም የሚመጥን መኾኑን አምነውበታል፡፡
በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ተወካዮች በፖርቹጋል ይካሄድ በነበረው የፊፋ ጉባዔ ላይ ተገኙ፡፡ የመገኘታቸው ዋነኛው ምስጢር ደግሞ አህጉራዊ እግር ኳስ ውድድርን ለመመስረት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ደቡብ አፍሪካም ነበረች፡፡ ከዚህ ጉባኤ በኋላ በ1949 ዓ.ም ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር የሚገናኙበትን፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት መድረክ የአፍሪካ ዋንጫን መሠረቱ፡፡
የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫም በሱዳን ካርቱም ተካሄደ፡፡ ወደ ፑርቹጋል ልዑኳን ልካ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማሟላት የሚገባትን ነገር ሳታሟላ በመቅረቷ ከካርቱሙ ድግሥ ተሰናበተች፡፡ ድግሡም በሦስቱ ሀገራት ደመቀ፡፡ ካርቱም የአፍሪካውያንን የመሰባሰቢያ ድግስ በመደገስ ቀዳሚዋ ከተማ ኾነች፡፡
ዛሬ ታላቅ ለኾነው የአፍሪካ ዋንጫ የሦስቱ ሀገራት ሚና የታሪክ መሠረት ነው፡፡ እነርሱ አፍሪካን አንድ የሚደርግ ጎጆ ቀደም ብለው ቀልሰዋልና፡፡ በሦስቱ ሀገራት የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ተወዳጅ እየኾነ መጣ፡፡ መሥራቿ ሀገር ኢትዮጵያም በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በንጉሧ ፊት አሸንፋ ዋንጫውን ሳመች፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሜዳቸው ተጫውተው፣ ድል አድርገው፣ የሀገራቸውን ሠንደቅ ከፍ ላደረጉት ልጆቻቸው ዋንጫውን አንስተው ሰጡ፡፡ ያም ቀን አስደሳቹ ነበር፡፡ በሜዳ ላይ ተጋድለው ሀገራቸውን ባለ ድል ያደረጉት የኢትዮጵያ ልጆች የድል ዋንጫውን በንጉሣቸው እጅ ተረክበዋልና ደስታቸው ወደር አልነበረውም፡፡ ንጉሡም ቢሆኑ ደስታቸው ኃያል ነበር፡፡
ዳሩ ከዚህ ዋንጫ በኋላ አረንጓዴ ባጫ ቀዩን ሠንደቅ አንግበው ወደ ሜዳ እየገቡ የተፋለሙት የኢትዮጵያ ልጆች የድል ዋንጫ የመረከብ እድል አልነበራቸውም፡፡ ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በኋላም የአፍሪካዋን ዋንጫ አንስቶ ለልጆቹ የሰጠ የኢትዮጵያ መሪ የለም፡፡ በእርሳቸው ዘመን ጀምረው፣ በእርሳቸው ዘመን ልጆቻቸው አሸንፈው፣ ዋንጫውን አንስተው የሰጡት ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ብቻ ናቸው፡፡
ከመሥራቾቹ ሀገራት መካከል ግብጽ በአፍሪካ ዋንጫ ላቅ ብላ ስትሄድ ኢትዮጵያና ሱዳን ከቤታቸው መራቅ ጀመሩ፡፡ የድል ዋንጫ ራቃቸው፣ ይባስ ብሎ ከድግሡ መሳተፍ ተሳናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የመሰረተችው የቤቷ ድግሥ እየራቃት 31 ዓመታት እንደ ዋዛ ነጎዱ፡፡ ለወትሮው አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ሲውለበለብ ልባቸው አብራ እየከነፈች በደስታ የሚዘሉት ኢትዮጵያውያን ሠንደቃቸውን በድግሡ ከሚውለበለቡት ሠንደቆች መካከል ፈልገው አጧት፡፡ ልባቸው ተሰበረች፣ እግርኳስን አይተው ሐሴት የሚያደርጉት፣ የሠንደቃቸውን ከፍ ማለት የሚመኙት እግር ኳስ ወዳዶቹ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካዋ ዋንጫ ሀገራቸውን ፈልገው አጧት፡፡ ቋንቋው ምንም ይናገር፣ ሃይማኖትም የትኛውን ያምልክ፣ ብሔሩም ከየትኛውም ይምጣ፣ ኢትዮጵያ ሠንደቋን አስቀድማ በ11 ልጆች ተወክላ ወደ ሜዳ ስትገባ ኹሉም በአንድ ድምጽ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እያለ በደስታ ይዛለላል፣ በሐሴት ያለቅሳል፡፡ ኹሉም ተረስቶ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ ይነግሣል፡፡ መግባቢያው ኢትዮጵያዊነት ይኾናል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ መሥራቿ ሀገር ኢትዮጵያ 31 ዓመታት ከራቀችበት የሚመልሷት ልጆች ትሻ ነበርና በድንቅ ልጆቿ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመሩት የኢትዮጵያ ብርቆች በድል ገስግሰው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ይዞ መዘመር የናፈቀውን ሕዝብ በደስታ አስለቀሱት፣ ሀገሩን በሙሉ በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ አጥለቀለቁት፡፡ ዋልያ፣ ዋልያ እያሉ እየዘመሩ፣ ኢትዮጵያውያን በፍቅር ሠከሩ፡፡
ታዲያ ይኽች የአፍሪካ እመቤት፣ የአፍሪካ ዋንጫ መሠረት ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪኳን እና የአህጉራዊውን ውድድር ደረጃ የሚመጥን ሜዳ የላትም ሲባል መስማት ያሸማቅቃል፡፡ ከኋላዋ ተነስተው ወደ አፍሪካ ዋንጫ የገቡት ሀገራት በዘመናዊ ሜዳዎች ሲዋቡ ኢትዮጵያ ግን ሜዳ አልባ ኾና ዘልቃለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ መዘጋጀቱ፣ ለዓለም ዋንጫም መታጨቱ ይቅርና የማጣሪያ ውድድሮቿን በሀገሯ እንዳታደርግ ተከልክላለች፡፡ ለምን ካሉ ዘመኑን የዋጀ ሜዳ የለሽም ተብላለችና፡፡ ሜዳ የሌላት የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች፡፡ ሜዳዎቿ ዘመኑን አይመጥኑም በመባላቸው ምክንያት ዋልያዎቹ በሀገራቸው የመጫዎት፣ ኢትዮጵያውያንም ልጆቻቸውን በስታዲዮም እያዩ የማበረታት እና የመደሰት እድል አላገኙም፡፡
ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ገመድ የሚያስተሳስረውን፣ በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ የሚያደምቀውን የፍቅር መንገድ እግር ኳስ ችላ ተብሎ ኖሯልና ኢትዮጵያውያን በሜዳችሁ አትጫወቱም ተባሉ፡፡
በሦስቱ ሀገራት የተመሠረተው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ላይ 24 ሀገራትን በአንድ ላይ ያሳትፋል፡፡ በየኹለት ዓመቱ በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ድግስ መቋደስ የሚሹት የአፍሪካ ሀገራትም ወደ ደግሱ ለመጓዝ ታላቅ ተጋድሎ ያደርጋሉ፡፡ በበቂ የተዘጋጀው ከደግሱ ይሳተፋል፣ የደከመው ደግሞ መጪውን ጊዜ ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ (ካፍ) በሜዳሽ መጫወት አትችይም የተባለችው ኢትዮጵያ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ እናያት ይኾን? እነዚያን የአፍሪካ ዋንጫ የደጋፊዎች ከዋክብት ዳግም በአረንጓዴ ጎርፍ ታጅበው ዋሊያ ዋሊያ ሲሉ እናይ ይኾን? ጊዜ ግን መልስ ይኖረዋል!
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/