‹‹ያ ጀብዱና ድል የጠገዴ፣ የወልቃይትና የአርማጭሆ ድል ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያንም ከመፈራረስ ያደነ ነው›› በቅራቅር ጀብዱ የፈጸመ ጀግና

0
481
‹‹ያ ጀብዱና ድል የጠገዴ፣ የወልቃይትና የአርማጭሆ ድል ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያንም ከመፈራረስ ያደነ ነው›› በቅራቅር ጀብዱ የፈጸመ ጀግና
ባሕር ዳር፡ የካቲት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ቤተ መንግሥትን የናፈቀ መደበቂያ ዋሻውን ተነጠቀ፡፡ ሳንጃ ቁርሳቸውን፣ ጎንደር ምሳቸውን ባሕርዳር እራታቸውን ለመብላት የጓጉ በዋሻ ውስጥ እንዲቆዩ ተደረጉ፡፡ ነፍጥ አንግቶ ያን ጀግና ሕዝብ አንገት አስደፍቶ በአንድ ቀን በርካታ ከተማዎችን መቆጣጠር መመኘታቸው የሚገርም ነበር፡፡ በሀሳባቸው መንገዱ ቀላል ሆነላቸው፣ ሲጀምሩት ከበዳቸው፣ የሀገሬው ሰው በነፍጥ ተቀበላቸው፣ ለፍቅር እንጂ ለጥል ሞሶብ አያቀርብምና፡፡
ዘላለማዊ የሆነ ምድራዊ ተድላ የለም፡፡ ከፈጣሪ ዙፋን ውጪ ሌሎች ዙፋኖች አላፊዎች ናቸው፡፡ አላፋ ጠፊ እስኪሆኑ ድረስም ጊዜ ያነሳው ይቀመጥባቸዋል፡፡ በተሰጠ ጊዜ በመልካም ተጠቅሞ ማለፍ ብልህነት፣ ጀግንነት፣ አርቆ አሳቢነት ነው፡
መልካም ሥም ‹‹ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር፣ ከአባት የሚሰጥ ወንበር›› ነው ይሉታል አበው፡፡ መልካም ሥም ሞቶ አይጠፋም፤ ዘላላማዊ ነው፡፡ በጦር ከተመራ ዘመን በፍቅር የተመራ ዘመን ይልቃል፡፡ ሁልጊዜ መገፋት መጥፋትን ያመጣል፤ የግፉዋን ፈጣሪ አለና፡፡
ከእርስቱ፣ ከጉልቱ፣ ከቤቱና ከንብረቱ የተፈናቀለው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ መመለሻው ናፍቆት ነበር፡፡ ትህነግ የወልቃይትን ጥያቄ ማዳፈን ተቀዳሚ ተግባሩ አድርጎት ነበር፡፡
አድራጊ ፈጣሪ የነበረበትም ቤተ መንግሥት ናፍቆታል፡፡ ያደረገው ሁሉ አልሆን ስላለው የመጨረሻው እድሉን ተጠቀመ፡፡ ጦር አንስቶ የሀገሩን ደጀን ወጋ፡፡ የትህነግ የእብሪት ጥግ ጫፍ ሲደርስ ነፍጥ ሲያነሳ በአማራ ክልል መጀመሪያ የተኩስ እሩምታ የተከፈተባት ቅራቅር ነበረች፡፡
ደጀኑን ወግቷል፣ የወንድሙን ቃል በልቷል፡፡ በደረቅ ሌሊት በቅራቅር ተኩስ ተጀመረ፡፡ ለማጥቃት ከተዘጋጀ እብሪተኛ ታጣቂ ጥይት ፈነዳ፣ የረጋው ሌሊት በጥይት ናዳ ተናወጠ፡፡ በሠላም ያድሩ ዘንድ የተመኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በጥይት እሩምታ ተቀሰቀሱ፣ የጥይት ውርጅብኝ ወረደ፡፡ ጊዜው ከባድ ነበር፡፡
‹‹ኧረግ አጅሬ የባሕር አዞ
አይወቀስም እጁን ተይዞ
እጁን ተይዞ ከሚወቀስ
መሞት ይሻላል አፈር መልበስ›› የሚባለው የጠገዴ ሕዝብ ነብር ሆኖ ተነሳ፡፡ እንደ አንበሳ አገሳ፡፡ እጅ መስጠት ነውር፣ ፈርቶ መሸሽ መሪር፣ ደፍሮ መግባት ክብር፣ ደረቴን እንጂ ጀርባዬን ጥይት አይመታው እያለ ተኩሱ ወዳለበት ይገገስግስ ጀመር፡፡ በዚያ አስቸጋሪ ሌሊት የተነሳውን የተኩስ ውሽንፍር ጀግኖች መከቱት፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በዓይን ጥቅሻ እየተግባቡ አስፈሪዋን ሰዓት አሳልፈዋል፡፡
የመጀመሪያዋ የትህነግ ጥይት በቅራቅር ላይ ከጮኸችበት ጊዜ ጀምሮ ጦር በመምራት፣ ራሱም በመውጋትና በማዋጋት ጀብዱ ከፈፀመው ጀግና ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡ አሥር ዓለቃ ዋኘው ምኅረቱ ይባላል፡፡ የጠገዴ ሰው የዋኘውን ሥም ጠርቶ አይጠግብም፡፡ በአንደበታቸው ይጠሩታል፤ በልባቸው ያመሠግኑታል፤ ስለ ጀግንነቱ ያወሩለታል፤ በስብዕናው ይገረሙበታል-አስር አለቃ ዋኘው፡፡
‹‹ይመጣ ጉሃላ፣ ይምጣ አርባያ፣ ይምጣ በለሳ
ጉድብ ሳይሠራ ከጠራው ሜዳ እጅ የሚያስነሳ›› ከተባለለት በለሳ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በለሳ ሲወለዱ በሰፊ አውድማ ሽንብራ ማፈስ፣ እያነጣጠሩ ሳይስቱ መተኮስ እንደ ልብ ነው፡፡
‹‹ሀገሬ በለሳ ኧረ መና ወንዙ
ውኃው ይጣፍጣል ማር እንደበረዙ›› እንደተባለ በለሳ ሲወድ ወትት፣ ፍትፍት፣ ጠጅና ጠላ ያቀርባል፡፡ ሲጠላ ደግሞ ጥይት ይሰጣል፡፡
አስር አለቃ ዋኘውም በዚሁ ቅኝት ነው ያደገው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ወታደር ሆኖ ሀገሩን ማገልገልና ጀብዱ መፈፀም ምኞቱ ነበር፡፡ ጊዜው ሄደ፡፡ የዋኘው ምኞት ይሳካ ዘንድ ያቺ ቀን ደረሰች፡፡ በ2003 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅሎ ብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ገባ፡፡ ወታደራዊ ስልጠናውን በብቃት አጠናቀቀ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገሩን ለማገልገል ቆርጦ ተነሳ፡፡ በዛልአንበሳ ግንባር ተመደበ፡፡ ለ8 ዓመታት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ቆየ፡፡
አስር አለቃ ዋኘው በሠራዊቱ የነበረውን ቆይታ ሲያስታውስ ‹‹እኔ የማውቀው ሕብረ ብሔራዊ ሠራዊት ነው፡፡ ስንሰለጥንም ሲዘመርልንም ደስተኞች ነበርን፡፡ በደስታ ነበር ትግሉን የተቀላቀልነው፡፡ በሥራ ዓለም ላይ ግን ማበላለጥ ነበር፡፡ የትህነግ የቅርብ ሰው ከሆነ ቁልፍ ቦታ ይቀመጣል፡፡ በ2008 ዓ.ም ትህነግ ጎንደር ላይ ሲጨነቅ እናንት ጎንደር የመጣችሁ ወታደሮች ሂዱና ጎንደር ያለውን ነገር አጣሩ፣ ከጎንደር ነው የመጣችሁ ስለ ጎንደር ንገሩን፣ በየቤተሰቦቻችሁ ምን አለ? ተብለን ተጠየቅን፡፡ እኔ ሕብረ ብሔራዊ ሠራዊት ነኝ፤ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ነው የማውቀው፤ ስለዚያ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለኝም አልኳቸው፡፡ ይህን በማለቴ እኔና አምስት ጓደኞቼ ያለ ምንም ምክንያት ስድስት ወራት ኩያ ላይ ታስረን ነበር›› ነው ያለን አስር አለቃ ዋኘው፡፡
ከልጅነቱ አንስቶ የሚወደው ሙያው ፈተና በዛበት፡፡ ዋኘው ከሚወደው ሙያው መሰናበትን መረጠ፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ወጣ፡፡ ሌላ የማኅበረሰብ አገልግሎት ጠበቀው፡፡ የአማራ ክልል ምልስ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ይፈልግ ነበርና ጥሪ ተደረገለት፤ በ2011 ዓ.ም ሚሊሻውን ተቀላቀለ፡፡
በጠገዴ ወረዳም የሚሊሻ ስምሪት መሪ ሆኖ ይሠራ ጀመር፡፡ በጠገዴ በቆየባቸው ጊዜያት የትህነግ ትንኮሳ ይገርመው ነበር፡፡ ‹‹ጠገዴ ከመጣሁ ጀምሮ ትህነግ የሚፈጥረው ትንኮሳ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ትልቅ ጥላቻ እንዳለው ማሳያ ሆነኝ›› ነው ያለው፡፡ መከላከያ ሠራዊት ላይ እያለም ትህነግ ባስቀመጣቸው ሰዎች ትልቅ ተፅዕኖ ይደርስባቸው እንደነበር ነግሮኛል፡፡ በመከላከያ ሠራዊት እያለ ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ አይችልም ነበር፡፡ የትህነግ የውስጥ ለውስጥ አካሄድ አድጎ መከላከያውን እስከ መውጋት ደረሰ፡፡
‹‹የጠሉት ይወርሳል የፈሩት ይደርሳል›› እንዲሉ ትህነግ የጠላው ሲጥለው፣ የፈራው ሲደርስበት መከላከያ ሠራዊቱን አድክሞ የአማራ ክልልን መቆጣጠር ዋነኛ ዓላማው ነበር፡፡ ዓላማውን ይፈፅም ዘንድ ያቀደውን አደረገ፤ መከላከያውን ወጋ፤ አልፎም የአማራ ክልልን ወጋ፡፡ የጠገዴ ሚሊሻና በጠገዴ የነበረው የአማራ ልዩ ኀይል የሚቀመስ አልነበረም፡፡ ‹‹የጠገዴ ሚሊሻ ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር በመቀናጀት በንቃት ነበር የምንከታተላቸው፤ ጳጉሜን ላይ ምርጫ ሲያካሂዱ ትንኮሳ ጀምረው ነበር፡፡ ትንኮሳው ወዲያው ቆመ፣ እኛ ምንም አንነካካም፤ እነርሱ ግን ትንኮሳውን ይፈልጉታል፤ በትንሽ ነገር ደምስሰነው ማለፍ እንችላለን ብለው ያስቡ ነበር›› ነው ያለው አስር አለቃ ዋኘው፡፡
ትህነግ በአማራ የፀጥታ መዋቅር ላይ የገመተውን ግምት እንደያዘ ጥቃቱን ጀመረ፡፡
‹‹ያን ጊዜ በሌሊት ጦርነት ሲጀመር
ምን አለ ጠገዴ ምን አለ ቅራቅር››
አስር አለቃ ዋኘው ያን ጊዜ ሲያስታውሰው ‹‹ጥቅምት 24 ምሽት ላይ ለወረዳው አስተዳዳሪ ስልክ ተደወለለት፡፡ ዳንሻ ላይ የነበረው ክፍለ ጦር በህወሃት ታፍኗል፡፡ ከእርሱ ያለው የፀጥታ ኀይል ንቁ ተባለ፡፡ የስልክ እንቅስቃሴ ደካማ ነበር፡፡ ለመገናኘት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ እንደ ሰማን ሚሊሻዎችን የመቀስቀስ ሥራ ጀመርን፡፡ ለልዩ ኀይሎችም መልዕክት አደረስን፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ በተጠንቀቅ ቆመ፡፡ ቅራቅር ለወታደር ገዢ መሬት ነው፡፡ ቅራቅርን ይዘው ከአርማጭሆና ከጎንደር የሚመጣውን ሠራዊት አንገት ለማስደፋት ነበር ዓላማቸው፡፡ የእኛ ኀይል በእነርሱ ልክ ትጥቅ አልነበረውም፡፡ ውጊያውን ጀመሩት፡፡ የእኛ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ሳይበገር በጀግንነት ያለ እረፍት ተዋጋ›› ነው ያለው፡፡
የትህነግ ታጣቂ ከማክሰኞ ገበያ እስከ ቅራቅር ያለውን ሥፍራ በድንጋይ ካብ ምሽግ በምሽግ አድርጎታል፡፡ የቡድን መሳሪያ ታጥቋል፡፡ ትህነግ ጥቃት ሲያደርስ የጠገዴ ሚሊሻና የአማራ ልዩ ኀይል በመከላከል ውጊያ ቀጥ አድርጎ ያዘው፡፡ ትህነግ ተጨነቀች፡፡ ለቁርስ ሳንጃ ልትደርስ የነበረችው አልሆን አላት፡፡ ፊት ለፊት የሚመጡት ታጣቂዎች የጥይት እራት እየሆኑ ቀሩ፡፡ ሌላ ኀይል ይጨመራል፤ እርሱም እንደዚያው ይሆናል፡፡ የሚሊሻውና የልዩ ኀይሉ ጉድብ በዋዛ የሚደረመስ አልነበረም፡፡ ውጊያው ጋለ፤ ጥይት እንደ ቆሎ ተቆላ፡፡
‹‹ጥይት ሲያጎራ ኪል ሲል ካርታ
ሆዱ አይሸበር ልቡ አይፈታ›› የጥይት በረዶ ሲዘንብ አስር አለቃ ዋኘው እና ጀግና ጓደኞቹ ሆዳቸው አይሸበርም፡፡ ሠዓቱ ነጎደ፡፡ እየደረሰ እየቀመሰ የሚመለሰው የትህነግ ኀይል ተስፋው እየተሟጠጠ መጣ፡፡ ጥይቱ እንዳጓራ ሌሊቱ ነጋ፡፡ የአርማጭሆ ጀግና እየበረረ ደረሰ፡፡ እስኪዚያው ግን የጠገዴ ሚሊሻና የአማራ ልዩ ኀይል ነበሩ ውርጅብኙን ያሳለፉት፤ ወጀቡን የመለሱት፤ ተስፋውን ያጨለሙት፡፡ የጠገዴ ሚሊሻ ገዢ ቦታዎችን በመያዝ አልነቃነቅ ብሎ ነበር ያደረው፡፡
‹‹ያ ሁሉ ውርጅብኝ እየወረደ የእኛ ሚሊሻ ከጉድቡ አያፈገፍግም፣ ጠላት አያሳልፍም፣ የሚወርደው የጦርነት ውሽንፍር ከባድ ስለነበር እኔ ራሴ እየመራሁ ገባሁ፡፡ ዘጠኝ ጊዜ ማጥቃት ፈፀሙብን እኛ ቦታችንን አለቀቅንላቸውም፤ ፍንክች የሚል ሰው አልነበረም፡፡ ሴቶች በነበረው አስደናቂ የመከላከል ውጊያ እልል እያሉ ያበረታቱን ነበር፤ ሞራል ሰጡን›› ነበር ያለው አስር አለቃ ዋኘው፡፡
ውጊያው ቀጠለ፤ የአርማጭሆና የጠገዴ ሚሊሻ ይፎክርና በሆታ ያቀልጠው ጀምር፡፡ የትህነግ ታጣቂ ከማፈግፈግ ውጪ አማራጭ አጣ፡፡ ጉድባቸውን የማያስደፍሩት፣ ጥይታቸውን መሬት ላይ የማይጥሉት፣ በዓይን ጥቅሻ የሚግባቡት፣ መከራም ቢጸና የማያፈገፍጉት ሚሊሻዎች እና ልዩ ኀይል ጠላትን ቆሉት፡፡ ቅራቅርን ሲመኝ የነበረው ወደ ማክሰኞ ገበያ መመለስ ጀመረ፡፡ ኀይሉን ያጠናከረው የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ጉድቡን እያስለቀቀ ይወጋው ጀመር፡፡ ከምሽግ ላይ ምሽግ ደራርቦ የነበረው እየጣለው ሮጠ፡፡ ማክሰኞ ገበያ ተያዘች፡፡
‹‹ከእርሱ ሲደርሱ ካልሆኑ ፈሪ
ነብስን ያሳጣል እንደ ፈጣሪ›› በጦር ስልቱ አጀብ የሚባልለት ዋኘውና ጓደኞቹ በፅናት ተከላክለው በኩራት ማጥቃታቸውን ተያያዙት፡፡ ከዚያ በኋላ አባራሪ ሆነው በየደረሱበት ምሽግ እያስለቀቁ፣ የተዋጋውን እየደመሰሱ፣ እጅ የሰጠውን ትጥቅ እያስፈቱ ይነዱት ጀመር፡፡ በጀግኖቹ ፊት የሚቆም ጠፋ፤ አካባቢው ነፃ ሆነ፤ ተከዜም ደረሱ፡፡
‹‹ባንዲራው ተከዜ ላይ ተተክሎ ካየሁት በኋላ ብሞት እንኳን አይቆጨኝም ነው ያልኩት፡፡ አሁን ደስተኛ ነኝ፡፡ ያ ጀብዱና ድል የጠገዴ፣ የወልቀይትና የአርማጭሆ ድል ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያንም ከመፈራረስ ያደነ ነው›› ነበር ያለው አስር አለቃ ዋኘው፡፡ ከድል በኋላም የጠገዴ ሚሊሻ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የነገረኝ፡፡ አሁን ካለበት ጥንካሬ የበለጠ ለማጠንከር እየሠሩ መሆናቸውንም ነግሮኛል፡፡
የትግል አጋሮቹ የዋኛውን ስም ጠርተው አይጠግቡም፤ ግርማው ያስፈራል፣ የልቡ ሙላት ያኮራል፣ የማይደነግጥ ልብ፣ የማይፈታ ወንድነት አለው፡፡ ለደጉ ሕዝብና ለእናት ሀገሩ በቅንንትና በፅናት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑንም ነግሮኛል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ