የ3ኛው ዙር የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎች የስፖርት ውድድር ተጀመረ፡

58
ባሕርዳር: መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ በሰባታሚት ማረሚያ ቤት የስፖርት ሜዳ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ፣ የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት፣ የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ለአንድ ወር የሚቆይ የታራሚዎች የስፖርት ውድድር ተጀምሯል፡፡
ውድድሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ የከፈቱት የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አብርሃም ተስፋ የውድድሩ ዓላማ የሕግ ታራሚዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማዘውተር ጤናማ እንዲሆኑ እንዲሁም እንዲዝናኑበት ታስቦ የሚዘጋጅ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ፕሮግራም መሳካት በገንዘብም ሆነ በተለያየ መንገድ እገዛ ላደረጉ ግለሰቦች እና ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶክተር ጋሻው ተሰማ ታራሚዎች በጤና፣ በአካል፣ በአዕምሮ እና በስነልቦና ጠንካራ ሁናችሁ ጊዜያችሁን ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣ በውድድሮች በመዝናናት እንድታሳልፉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ውድድሩ የሚከናወነው በመረብ ኳስ፣ በገመድ ጉተታ እና በእግር ኳስ ሲሆን በመረብ ኳስ ጨዋታ ላሸነፉ ቡድኖች የማረሚያ ቤትቶች ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር አባይነህ በላይ የአሸናፊነት ዋንጫ መሰጠቱን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!