“የፈረስ ባሕላዊ ስፖርት በትኩረት ተሠርቶበት አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መኾን ይገባዋል” ፈረሰኛዋ ጥሩዓለም ትኩየ

359
ደብረታቦር: ጥር 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ዘንጃ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለደች። የ23 ዓመት ታዳጊ ናት። በአባቷ ቤት ፈረስ እንደማይጠፋ የምትናገረው ጥሩዓለም ከልጅነቷ ጀምሮ ፈረስ እየጋለበች ነው ያደገችው።
የፈረስ ጉግስን ከአባቷ እንደወረሰችው ትናገራለች። አባቷ ፈረስ እንድትጋልብ ሙሉ ፈቃድ ይሰጧታል። አባቷ ጉዞ ሲወጡ ፈረሳቸውን ሸልማ የመሸኘት ልምድ እንዳላትም ነግራናለች።
እንደ ጥሩዓለም ገለጻ አሁን ላይ የፈረስ ሽርጥ ባሕላዊ ስፖርትን ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች። አገር አቀፍ የሴቶች የፈረስ ሽርጥ ውድድር ተሳታፊም ናት። በተለያዩ አካባቢዎች በተሳተፈችባቸው ውድድሮችም አሸናፊ እንደኾነች አጫውታናለች። ሶስት ወርቅ እና ስድስት ብር ሜዳሊያ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያ ተሸልማለች። ከወረዳ እስከ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ለአብነትም ደብረታቦር፣ እንጅባራ፣ ደብረማርቆስ፣ ደሴ እና ምንጃር ላይ ተወዳድራለች። ደብረ ማርቆስ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ሲኖራት ደብረታቦር ላይ ደግሞ ሁለት ወርቅ አላት።
አገው ምድር ላይ የፈረስ ስፖርት ተፎካካሪ ሴቶች አሉ የምትለው ፈረሰኛዋ በርካታ ሴቶች ወደ ባሕላዊ የፈረስ ስፖርት መምጣት አለባቸው ብላለች። ፈረስ መጋለብ ተወዳጅ ባሕላዊ ስፖርት ቢኾንም የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠውም ተናግራለች። ጥሩዓለም “ለፈረስ ስፖርት ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ዘርፍ እንዲኾን መሥራት ይገባል” ስትል ገልጻለች።
ፈረሰኛዋ ወደፊትም የዘርፉ ጠንካራ ተወዳዳሪ ኾና የመቀጠል ፍላጎት አላት። ከጥር 30 እስከ የካቲት 16/2015 ዓ.ም በሚዛን ቴፒ በሚኖረው የፈረስ ሽርጥ ውድድር ላይ እንደምትሳተፍም ገልጻለች። በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ ለመኾን በዝግጅት ላይ እንደምትገኝም ተናግራለች።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!