ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት “የጥጥ፣ የቴክስታይል እና የአልባሳት እሴት ሰንሰለት በአፍሪካ” በሚል መልዕክት ለ11ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በባሕርዳር ተካሂዷል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር አበራ ከጪ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍን የተመለከተ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ዶክተር አበራ ዘርፉ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ትልቅ አቅም አለው ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለተደረጉ የኢኮኖሚ ሽግግሮች ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ተሞክሮ ያለው ዘርፍ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ቻይና፣ ባንግላድሽ እና ቬትናም በዓለም ላይ ዘርፉን በመምራት ኢኮኖሚያቸውን ያሳደጉ ሀገራት መኾናቸውን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ባንግላድሽ እና ቬትናም ዘርፉን በመጠቀም ወደ መካከለኛ ገቢ የተሸጋገሩ ሀገራት ናቸው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ትኩረት ቢሰጠውም በተቀናጀ መንገድ መሠራት ባለመቻሉ ለውጥ አለመምጣቱ ተገልጿል፡፡ ዘርፉ የወሰደው ጊዜ ከአደጉት ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲታይ ግብርና ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚ ወደ መካከለኛ ገቢ የሚያሸጋግር ጊዜ ላይ እንደኾነ ተብራርቷል፡፡
ዘርፉ ከፍተኛ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የሥራ ዕድል መፍጥር የሚችል እና ትልቅ የገበያ ፍላጎት ያለው በመኾኑ በመጀመሪያ ዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ተብሏል፡፡ ሀገሪቱን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሸጋገር ከተፈለገ ዘርፉን እንደገና በፖሊሲ መቃኘት ያስፈልጋል ብለዋል ዶክተር አበራ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባለፈ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ ባንኮች በገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ጥጥ የማምረት አቅም ቢኖራትም እስከ አሁን ማምረት የተቻለው 3 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የሚመረተው ምርትም የጥራት ችግር እንዳለበት ነው ተመራማሪው ያነሱት፡፡
በውይይቱ ላይ በጥጥ፣ በጋርመንት፣ ፋሽን እና ሌዘር መስኮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በመጡ ተመራማሪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ቀርቧል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!