የጥፋት ባላደራዎቹ!

0
222

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅት አይቶ እና አዝማሚያ ለክቶ የመከራ ዶፍ የሚወርድባት ኢትዮጵያ ዛሬም የንጹሃን ደም በከንቱ ከመፍሰስ አላባራላትም፡፡ ከማጀት እናቶች፣ ከሜዳ ሕጻናት፣ ከእርሻ ቦታ አባቶች እና ከበራፍ አዛውንቶች በጥፋት አሩር የሚለቀሙባት ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ አለች፡፡ የእብድ ገላጋይ በዝቶ እና ካለፈው የሚማር ጠፍቶ የስንቶች ደም ደመ-ከልብ ኾነ፡፡ ትንሽ ወደፊት ስትራመድ በብዙው ወደ ኋላ የሚመልሳት የፍቅር ዐይነ ጥላ ያልተገለጠላት ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ አለች፡፡
የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ አንድ ልብ መስካሪ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ በቅንጅት ተናበው የሚፈጥሩትን የጥፋት ድግስ በዙሪያቸው ኾነን እንድንሞቅ ዛሬም እየጋበዙን ነው፡፡ በሩዋንዳዊያን ላይ ጽናትን እና አንድነትን የፈጠረው የእንግሊዛዊያን ስላቅ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚሠራበት ጊዜ መቼ እንደኾነ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
የዛሬ 29 ዓመታት ገደማ 800 ሺህ ይደርሳሉ የተባሉ ሩዋንዳዊያን በ100 ቀናት ውስጥ እርስ በእርሳቸው ተጨፋጨፉ፡፡ ቱትሲዎች በሁቱ ወንድሞቻቸው መራር የተባለውን የሞት ጽዋ ተቀበሉ፡፡ እድል የቀናቸው ደግሞ ቀን ከሌት በጫካ እና በባሕር ላይ ተጉዘው ጎረቤት ሀገራት ድንበር ደረሱ፡፡ ከሞት ያመለጡት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያ ኾነው የወገኖቻቸውን ሃዘን በእምባ እና ርሃብ ተወጡ፡፡
በሩዋንዳ ሰማይ ስር ለዘመናት ተዋደው የኖሩት ሁለት የአንድ እናት ብሔሮች እርስ በእርሳቸው ተጨካከኑ፡፡ የጥላቻ ሰይፎች እናቶችን፣ ሕጻናትን እና አረጋዊያንን ሳይመርጡ በንጹሃን አንገት ላይ ክፉኛ ተሰነቀሩ፡፡ ጥላቻው የመነጨው ከውስጣቸው ሳይኾን ከቅኝ ግዛት ዘመን ጦስ ይመዘዛል፡፡ ቤልጂየሞች በፍቅር የኖሩትን ሩዋንዳዊያንን እርስ በእርሳቸው በጥላቻ እና በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርገዋቸው አለፉ፡፡
ጥላቻ ያድጋል፣ ጥላቻ ይሰፋል፣ ጥላቻ ይተላለፋል፣ ጥላቻ ይጎመራልና ሩዋንዳዊያን የተዘራላቸው የጥላቻ ዘር በብዙው አፍርቶ የመከራ አዝመራው የሚሰበሰብበት ወቅት ደረሰ፡፡ ሚያዝያ 6/1994 (እ.አ.አ) የዘር ሐረጋቸው ከሁቱ ብሔር የሚመዘዘው እና የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁቨናል ሀቢያሪማናን እና የቡሩንዲው አቻቸውን ሳይፕሪያን ንታያሚራን የያዘችው አውሮፕላን ተመትታ በመውደቋ ፕሬዚዳንቶቹ እና የጉዞው አባላት ሕይዎታቸው አለፈ፡፡ ያ የሩዋንዳዊያን የመከራ ሦስት ወር ከዚያች እለት ጀምሮ አንድ አለና 100 ቀናትን አስቆጠረ፡፡ የሩዋንዳዊያን ምድር ሲኦልን ተክታ በጥላቻ፣ በጭካኔ እና በደም ጎርፍ አሳለፈች፡፡
ያ ክፉ የጥላቻ መንፈስ ከ100 ቀናት በኋላ ግን ከኪጋሊ፣ ከመካከለኛው እና ከደቡባዊ የሩዋንዳ ግዛቶች ተገፈፈ፡፡ በጥላቻ ፈረስ የሚጋልቡ ልቦች መስከን ሲጀምሩ በስህተቶቻቸው የተሰበረ ልብን ተሸከሙ፡፡ የሞቱትን መመለስ ባይችሉ እንኳን ዳግም በሩዋንዳ ምድር መሰል ጥፋቶች አንዳይፈጸሙ የሚያስችል የይቅርታ ነፋስ በዙሪያቸው ናኘ፡፡ ከምንም በላይ ባንክም ታንክም እያቀረቡ ሲያጫርሷቸው የነበሩ ውጫዊ ኃይሎች ምጸት ሩዋንዳዊያንን እንደ ብረት አጸናቸው፡፡
በሩዋንዳዊያን የርስ በእርስ ጭፍጨፋ የሰማይ አሞራዎች እና የአካባቢው ውሾች ከመቼውም ጊዜ በላይ በልጎላቸው ከረሙ፡፡ በየሜዳው የወደቁ አስከሬኖችን አንስቶ መቅበር ቅንጦት የሆነባት ሩዋንዳ ለውሾች እና ለሰማይ አሞራዎች ሲሳይ ኾኑ፡፡ ከእርስ በእርስ እልቂቱ ማግስት በሰው ልጅ ስጋ እና አጥንት የደለቡ ውሾች ከሞት ለተረፉት ሩዋንዳዊያን መጥፎ የህሊና ደወል እየኾኑ ረበሿቸው፡፡
የደለቡ ውሾችን ማየት ያንን ከፉ የመከራ ዘመን ማስታዎስ እየኾነባቸው ሩዋንዳዊያን ተቸገሩ፡፡ እናም ጥላቻን ለመበቀል ቆርጠው የተነሱት እና በወገኖቻቸው ሞት የተሰበረ ልብ የያዙት ሩዋንዳዊያን የደለቡ ውሾችን መግደል ይጀምራሉ፡፡ ያኔ ነበር መሰረታቸው ከምዕራባዊያን ሀገራት በተለይም ከእንግሊዝ የኾኑ ለጋሽ ድርጅቶች የውሾች ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ሲሉ መጮኽ የጀመሩት፡፡
የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ሲረግፍ ትርጉም ያልሰጣቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ውሻ ሲሞት ማላዘን ጀመሩ፡፡ ይኽ ለሩዋንዳዊያን የማንቂያ ደወል ኾኖ አገለገላቸው፡፡ ያ ስላቅ ለሩዋንዳዊያን ጽናትን እና አንድነትን ፈጥሮላቸው በ2003 (እ.አ.አ) የብሔር ልዩነትን እውቅና ለነፈገው ሕገ-መንግሥት መጽደቅ ዐቅም ኾናቸው፡፡
ጥያቄው ጽንፍ የረገጠ የብሔር ልዩነት ለሚያምሳትና ለንጹኀን ሞት መበራከት ኢትዮጵያ መድኃኒት የምታገኘው መቸ ይሆን? ኢትዮጵያዊያን በየወቅቱ የግል ጥቅም እና ዝና የሚንጣቸው የግጭት ነጋዴዎች በሚፈጥሩት መከራ የንጹሃን ደም ዋጋ እና መስዋእት ኾኖ የሚቀርበው? መቼ ነው ኢትዮጵያዊያን የጥፋት ባላደራዎች በሚፈጥሩት ወከባ በሀገራቸው ያለስጋት እና ያለሰቀቀን ሠርተው የሚኖሩት? ያንን ቀን ንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ይናፍቁታል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/