“የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል” የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት

49
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕርዳር: ጥር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በኩረ ትጉኃን ዘራዳዊት ኃይሉ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ጥምቀትን በጎንደር “በርካታ የሀገር ውስጥና የባሕር ማዶ እንግዶች የሚታደሙበት ነው።ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓጋል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንግዶቻችን ያለምንም ስጋት ጥምቀትን በጎንደር አክብረው እንዲመለሱ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ፣በሰላምና በአብሮነት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ እንደ ሃይማኖት ተቋም ከ13 በላይ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ እንደገቡ ነው የተናገሩት።
ለጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ መዋል የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ፤ ለዚህም ከወጣቶች ጋር በቅንጅት መሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ለጥምቀት በዓል የታቦታቱን ክብር የሚጠብቁ፣ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ሥርዓት የሚያስከብሩ ወጣቶች አሉን ነው ያሉት።

የከተማዋ ነዋሪዎች በየቤታቸው እንግዶችን ተቀብለው ማረፊያ ለመስጠት ፈቃደኛ የኾኑ መመዝገባቸውንም አንስተዋል። ከየትኛውም የዓለም ዳርቻ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጣ ሁሉ የማረፊያ ቦታ ችግር ስጋት አይኾንበትም ብለዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ እንግዶችን እንዲያስተናግድ፣ አብርሃማዊ ጥሪ በማድረግም ወደ የቤታቸው እየጋበዙ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣም አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!