የጥምቀቱ አድማቂዎች!

48
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የጥምቀት በዓል አንዱ ነው። በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ ጎንደር አንዷ ናት።

በዓሉ በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ ካላቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ዋናዎቹ በከተማው በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች የባሕል አልባሳትን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የአካባቢ ጽዳት የመጠበቅ፣ እንግዶችን የመቀበል፣ በበዓሉ ጊዜ ደግሞ ታቦታቱን የማጀብና የአካባቢውን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠሩ ነግረውናል።

ካነጋገርናቸው የወጣቶች አደረጃጀቶች መካከል የቅዱስ አስጢፋኖስ የፅዋና የመረዳጃ ማኅበርና ደራሽ በጎ አድራጎት አንዱ ነው። ማኅበሩ ከ300 በላይ አባላት አሉት፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር ሲሳይ መስፍን ማኅበሩ ሲመሠረት ሃይማኖታዊ ክንውኖች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል። በወቅቱ በጥምቀት በዓል ባሕላዊ አልባሳትን በመልበስ አካባቢውን የማስተዋወቅ፣ ታቦታቱን በዝማሬ ማጀብ፣ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ ባሕላዊ ጭፈራዎችን የማስጨፈር እና ደንብ የማስከበር ሥራ ይሠሩ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

የዘንድሮው የጥምቀት በዓልም በድምቀት እንዲከበር ወጣቶቹ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ መኾናቸውን ነግረውናል። አካባቢዎችን ማስዋብ ሥራም እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ እንግዶች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ቅርሶችን እንዲጎበኙ የማመቻቸት ሥራም እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ከ14 ዓመት በፊት የጥምቀትና ሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር የተመሠረተው ማኅበር ተግባሩን በማስፋት አሁን ላይ አቅመ ደካሞችን የማገዝ፣ በገንዘብ ችግር መታከም ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግና በሌሎች ማኅራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ የአድዋ ድል ቀን ሲከበርም በተለያዩ ዝግጅቶች በዓሉን ይዘክራሉ፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት በጎንደር የጥምቀትን በዓል ለመታደም በርካታ ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ ይገባሉ፡፡ በመኾኑም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ የተለያዩ የወጣቶች ማኅበራት ጋር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹልን። ለዚህም ከ3 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች የተለዩ አልባሳትን በመልበስ ታቦታቱን በማጀብ ሥርዓት የማስከበር ሥራ የሚሠሩ ይኾናል፡፡ አኹን ላይም ወጣቶቹ የአካባቢ ጽዳት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የነገሩን፡፡

በከተማ አስተዳደሩ እንግዶችን ተቀብለው የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚያስጎበኙ ከ74 በላይ ወጣቶች ተለይተዋል፤ 86 ወጣቶች በፎቶ ማንሳት ተደራጅተዋል፤ በባሕላዊ ምግብ ዝግጅት የሚሳተፉ ከ300 በላይ ወጣቶች ተለይተዋል፡፡ በባለፈው ዓመት ከ326 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ጥምቀትን ለማክበር በጎንደር ታድመዋል። በዚህ ዓመትም እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ጎብኝዎች የጥምቀት በዓልን ለማክበር ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!